የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋምቤላ ከተማ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያ፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ዘረፋ የፈፀሙ፣ ድርጊቱን የመሩና ሲያስፈጽሙ የነበሩ ኃላፊዎች በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ አቀረበ።
ኮሚሽኑ መስከረም 18 ቀን 2015 ባወጣው ባለ 13 ገፅ የምርመራ ሪፖርቱ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ታጣቂ ቡድን (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ)፣ የጋምቤላ ነፃነት ግንባር ታጣቂ ቡድን፣ የጋምቤላ ክልል ልዩ ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ ሚሊሻዎች እና ተባባሪ ወጣቶች የድርጊቱ ተሳታፊዎች መሆናቸውን አመልክቷል።
በሰላማዊ ሰዎቹ ላይ ግድያዎች፣ የአካል ጉዳቶችና የንብረት ዘረፋዎች የደረሱት በጋምቤላ ከተማ ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች፣ በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) እና በጋምቤላ ነፃነት ግንባር (ጋነግ) መካከል የተደረገው ውጊያን ተከትሎ ከሰኔ 7 እስከ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በክልሉ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እንዲሁም ታጣቂ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎች እንደሆነም አስረድቷል።
ኢሰመኮ የመብት ጥሰቶችን የፈጸሙ ሰዎችና ቡድኖችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥ የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ተጎጂዎች ፍትሕ እና ተገቢውን የካሳና መልሶ መቋቋም ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል እንዲረዳ ያከናወነውን ምርመራ፣ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦች በሪፖርቱ አካትቶ አቅርቧል።
የአየር ጥቃት
የኤርትራ አየር ኃይል በሰነዘረው የአየር ጥቃት ለጊዜው ቁጥራቸው ተለይቶ ያልተገለጠ የምዕራብ ትግራይ አዲ ዳዕሮ ሰላማዊ ነዋሪዎች ለሕልፈተ ሕይወትና የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው መሆኑን ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው።
አደጋው በነዋሪዎቹ ላይ የደረሰው መስከረም 17 ቀን 2015 መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፤ ጥቃቱን አስመልክቶ በኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታትም ሆነ በሕወሓት በኩል እስካሁን የተሰጠ ይፋ መግለጫ የለም።