የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ኤፕሪል 29 ባወጡት መግለጫ በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥትና በሕወሓት በኩል እየተወሰዱ ያሉ የጊዜያዊ ግጭት ማቆምና ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች አበረታች መሆናቸውን በማንሳት፤ በድርድር ላይ ወደ ተመሠረተ ተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ አጋጣሚውን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
አቶ ብሊንከን በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለምግብ ዋስትና እጦትና ለረሃብ መጋለጥ መቀጠል የግጭቱ ቀጥተኛ ውጤት መሆኑን አመላክተዋል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥም ለትግራይና አፋር ተጎጂ የማኅበረሰብ አባላት የረድዔት ምግብ ማቅረብ መቻሉ ያበረታታቸው መሆኑን አንስተው፤ ጥረቶቹንም በግጭቱ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ተደራሽነት እንዲኖር አክሎ ማስፋት እንዲቻል የኢትዮጵያ መንግሥትንና የክልሉን ባለስልጣናት እንደሚያበረታቱ ገልጠዋል።
በቅርብ ወራት ውስጥም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግጭቱ እንዲያበቃ፣ የአስቸኳይ ጊዜያዊ አዋጅ እንዲነሳ፣ የተወሰኑ የፖለቲካ እሥረኞችና ታጋቾ እንዲለቀቁ የማድረግ ተከታታይ የሆኑ አበረታች እርምጃዎች የወሰዱ መሆናቸውን አንስተዋል።
አያይዘውም፤ የትግራይ ባለስልጣናት የግጭት ማቆም እርምጃ ይፋ ማድረጋቸውንና አብዛኛዎቹም ኃይሎቻቸውንም ከአፋር በማስለቀቅ ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የማያመነቱ መሆናቸውን እንዳሳዩ ገልጠዋል።
ሆኖም የአቶ ብሊንከንን መግለጫ ለማረም የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ የሕወሓት ጦር "ሙሉ በሙሉ" አፋርን ለቅቆ እንደወጣ ገልጠዋል።
በተቃራኒው የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሕወሓት "ከአፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች እንዲወጣ" መንግሥት ጥሪ የሚያቀርብ መሆኑን በሚያዝያ 15 መግለጫው አስታውቋል።