ደቡብ ኮሪያ መዲና ሴኡል የሃለዊን በዓል በማክበር ላይ የነበሩ 149 ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ 76 ለመቁሰል አደጋ ተዳርገዋል።
ከቆሰሉት ውስጥ 19ኙ ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ከሟቾቹ ውስጥ ሁለቱ የውጭ አገር ዜጎች ናቸው።
የሃለዊን አክባሪዎቹ ለአደጋ የተጋለጡት በምሽት ሕይወት ድምቀቷ አያሌዎችን በምትስበው ኢታኢዎን ጠባብ ጎዳና ላይ ከምሽቱ 10 pm በተፈጠረ መጨናነቅ ነው።
የአካባቢው ባለስልጣናት አደጋው እንደምን እንደደረሰ በምርመራ ላይ ያሉ መሆኑን ገልጠው፤ በአደጋው የተጎዱ ሰዎች ቁጥር እንደሚጨምር ያላቸውን ስጋት አስታውቀዋል።
ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በብራዚል
ብራዚላውያን ዛሬ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ከቀረቡት ዕጩዎች አንዳቸውን በአብላጫ ድምፅ ይመርጣሉ።
ለዳግም ውድድሩ የቀረቡት የወቅቱ ፕሬዚደንት ጃይር ቦልሶናሮ እና የቀድሞው ፕሬዚደንት ሊዊዝ ሉላ ዳ ሲልቫ ናቸው።

የሁለቱም ዕጩዎች ደጋፊዎች በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ በመዲናይቱ የምርጫ ዘመቻ ማጠቃለያ ሰልፍ አካሂደዋል።

ሁለቱም ዕጩዎች ከወዲሁ አሸናፊ እንደሚሆኑ በመግለጥ ደጋፊዎቻቸው እያበረታቱ ነው።
ምርጫው ብርቱ ታሪካዊ ፉክክር የታየበት ሲሆን፤ ለብራዚል መፃኢ ዕድል በእጅጉ ወሳኝ ነውም ተብሎለታል።

