የአውስትራሊያ የበጋ የቀን ብርሃን ቁጠባ ሰዓት ቆጠራ ለውጥ ከነገ እሑድ 2 am ኦክቶበር 1 / መስከረም 20 አንስቶ ይጀምራል።
አገረ ግዛቷ 7.7 ሚሊየን ስኩየር ኪሎሜትሮችን አቅፎ በመያዝ ከዓለም በመጠነ ሰፊነቷ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አውስትራሊያ የሰዓት ቆጠራ ዞኖቹዋ በሶስት የተከፈሉ ናቸው።
አውስትራሊያ ውስጥ የቀን ብርሃን ቁጠባ የሰዓት ቆጠራ ለውጥ የሚካሔደው በኒው ሳውዝ ዌይልስ፣ ቪክቶሪያ፣ ደቡብ አውስትራሊያ፣ ታዝማኒያ፣ የአውስትራሊያ መዲና ግዛትና ኖርፎክ ደሴት ሲሆን፤ በኩዊንስላንድ፣ ሰሜናዊ ግዛት፣ ምዕራብ አውስትራሊያ፣ ክሪስማስ ደሴት ወይም ኮኮስ ደሴቶች አይከናወንም።
በወርኃ ኦክቶበር የመጀመሪያው ሳምንት እሑድ አንድ ሰዓት ወደ ፊት በመቅደም 2am የሚጀምረው የቀን ብርሃን ቁጠባ የሰዓት አቆጣጠር ለውጥ በወርኃ ኤፕሪል የመጀመሪያው እሑድ 3am ላይ አንድ ሰዓት ወደ ኋላ በመመለስ ያበቃል።
ሰሜን ጎንደር ዞን
በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን በተከሰተው ድርቅ ሳቢያ 452 ሺህ ነዋሪች ለጉዳት የተጋለጡ ሲሆን 220 ሺህዎቹ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያሻቸዋል።
የተጎጂዎችን ቁጥርና የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጠኑን ያስታወቀው የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው፤ ጉዳቱ የደረሰባቸው አካባቢዎች ጃናሞራ፣ ጠለምት፣ የበየዳ ወረዳዎችን ጨምሮ፤ ምሥራቅና ምዕራብ ጠለምት፤ እንዲሁም የደባርቅ አካባቢዎችን ያካተተ ነው።
ድርቁ ባስከተከለው ጉዳት ሳቢያም በ19,500 ሔክታር በተዘሩ ሰብሎች ላይ ጉዳት ደርሷል።