አምነስቲ ኢንተርናሽናል
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኖቬምበር 12 ይፋ ባደረገው መግለጫው ኖቬምበር 9 ምሽት በትግራይ ክልል ማይ ካድራ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በስለት ተወግተው ወይም ተቆራርጠው ሕይወታቸው የጠፋ መሆኑን አስታውቋል።
የድርጅቱ የቀውስ ማስረጃ ምርመራ ላቦራቶሪ ምርመራ አካሂዶ በዲጂታላዊ መንገድ እንዳረጋገጠው በአሰቃቂ ሁኔታ ከተገደሉ በኋላ በከተማዋ ተጥለው የተገኙና በስትሬቸር ሲጓጓዙ የሚታዩ የአስከሬኖች ፎቶዎችና ቪዲዮዎች የቅርብ ጊዜያት መሆናቸውን ገልጧል።
"ቁጥራቸው በጣም የበዛ ሰላማዊ ሰዎች መጨፍጨፋቸውን አረጋግጠናል። የጭፍጨፋው ሰለባዎች ከግጭቱ ጋር ምንም አይነት ወታደራዊ ግንኙነት ያልነበራቸው የቀን ሠራተኞች ሆነው አግኝተናቸዋል። በትግራይ ያለው የመገናኛ ዘዴ የተዘጋ በመሆኑ የዚህን ቅስም ሰባሪና አሰቃቂ ክስተት ትክክለኛ የጉዳት መጠንና ስፋት ማረጋገጥ የሚቻለው ጊዜ ሲፈቅድ ብቻ ነው" ሲሉም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር ዴፕሮዝ ሙቼና ተናግረዋል።
ዳይሬክተሯ አያይዘውም “መንግሥት በሥፍራው እያካሄው ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ በሚመለከት ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም የረድኤትና የሰብዓዊ መብት ተመልካች ድርጅቶች በሥፍራው ስላለው ሁኔታ ያልተገደበ መረጃና ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማስቻል በትግራይ ያለውን የመገናኛ አውታሮችን ሥራ ወደነበረበት እንዲመልስ” ሲሉ ጠይቀዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቱ አምነስቲ ከዓይን ምስክሮችና ከደረሱት የተረጋገጡ የፎቶ ማስረጃዎች እንደተረዳው “አብዛኞቹ አስከሬኖች ወድቀው የተገኙት በከተማዋ ማዕከል በንግድ ባንክ አቅራቢያና ጎረቤት ከተማ ወደሆነችው ወደ ሁመራ በሚያስወጣው መንገድ ግራና ቀኝ” እንደነበረና “አስከሬኖቹ ቢላዎና ቆንጨራ በመሰሉ ስለታማ መሳሪያዎች በተፈፀሙ ጥቃቶች የተቆራረጡ” መሆኑን ከዓይን ምስክሮችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባሰማራቸው ገለልተኛ ፓቶሎጂስቶች መረጋገጡንም አስታውቋል።
የጭፍጨፋውን ፈፃሚዎች በሚመለከት አምነስቲ ኢንተርናሽናል ማንነታቸውን ለማረጋገጥ እንዳልቻለ ጠቅሶ ሆኖም ከዓይን እማኞች እንደተረዳው የጅምላ ጭፍጨፋው የተፈፀመው “የትሕነግ (ትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር) ታማኞች” መሆኑንና ድርጊቱ የተፈጸመውም በፌዴራል የመከላከያ ኃይል ሽንፈት ከደረሰባቸው በኋላ እንደነበር መረዳቱን አስታውቋል።
ጭፍጨፋውን አስመልክቶ ዳይሬክተር ዴፕሮዝ ሙቼና "ይህን በንፁሃን ላይ የተሰነዘረ አረመኔያዊ ጥቃት በሚመለከት የኢትዮጵያ መንግስት ሳይውል ሳያድር ዝርዝር፣ ገለልተኛና ውጤታማ ምርምራ አድርጎ ፈፃሚዎቹን ለፍትሃዊ ፍርድ ማቅረብ አለበት" ሲሉ አስቸኳይ ጥሪ አቅርበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን
በሌላም በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ማይ ካድራ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ያሳሳሰባቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ለጊዜው ተፈጸመ የተባለውን የጅምላ ጭፍጨፋ ዝርዝር ሁኔታ አስመልክቶ የቀረበው ሪፖርት በአምነስቲ ኢንተርናሽናል ብቻ በመሆኑና ሙሉ በሙሉ ስላልተረጋገጠ የተሟላ ምርመራ እንዲደረግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ኮሚሽነሯ አያይዘውም “ድርጊቱ በአሁኑ ወቅት በውጊያ ላይ ባለው አንድ ቡድን ሆን ተብሎ የተፈጸመ ከሆነ፤ እርግጥ ነው እኒህ የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎች ወደ ጦር ወንጀሎች ስለሚያቀኑ ለተፈጸመው ድርጊት ገለልተኛ የሆነ ምርመራንና ሙሉ ተጠያቂነት ግድ የሚል ነው” በማለት “ይሁንና በአሁኑ ወቅት ቀዳሚው ተግባር ተጨማሪ ግድያዎች ከመከሰታቸው በፊት ውጊያውን ማስቆም ነው” ብለዋል።
በማከልም ከተለያዩ ምንጮች የሚያገኟቸው መረጃዎችን ለማጣራት አዋኪ መሆኑን ጠቅሰው “አስፈላጊ የሆኑ የውኃና መብራት አቅርቦቶች በተጨማሪም የግንኙነቶች መቋረጥ እንዲሁም የምድርና አየር ተደራሽነት የመዘጋት ሪፖርቶች በእጅጉ አሳስቦኛል” ሲሉ ያደረባቸውን ስጋት ገልጠዋል።
ዩናይትድስቴትስ
ይህ በእንዲህ እንዳለም የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ በማይ ካድራ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ መንግሥታቸው ማውገዙን ሲያስታውቁ “በማይ ካድራ ሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ እናወግዛልን እንዲሁም ትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄደው ግጭት እንዲያበቃና እንዲበርድ አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወሰዱ አበክረን እናሳስባለን” ያሉ ሲሆን፤ በማከልም “የሰላም ዳግም መስፈንና የሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ማግኘት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።