አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዛሬ ኦገስት 11, 2021 ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ትስስሮሽ ባላቸው ኃይሎች ከትግራይ ግጭት ጋር ተያይዞ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት መፈጸሙን ገልጧል።
ሪፖርቱ በወሲባዊ ጥቃት ተሳታፊነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ መከላከያ ኃይል፣ የኤርትራ መከላከያ ኃይል፣ የአማራ ክልል ፖሊስ ልዩ ኃይልና የፋኖ ሚሊሺያ ቡድንን በስም ጠቅሶ አስፍሯል።
ሪፖርቱ 63 ወሲባዊ ጥቃት ሰለባዎችንና የሕክምና ባለሙያዎችን ያነጋገረ መሆኑን የገለጠ ሲሆን፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ አግነስ ኮላማርድ በበኩላቸው "የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይላትና አጋር ሚሊሺያ አባላት ወሲባዊ ጥቃቶችን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ አስቸኳይ እርምጃ መውሰድ አለበት፤ የአፍሪካ ኅብረት ያላንዳች ዝንፈት ግጭቱን ለአፍሪካ ኅብረት እና ፀጥታ ምክር ቤት ማቅረብ ይገባዋል" በማለት አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በወሲባዊ አመፅ ተግባር ተሳትፈዋል ተብለው በተጠረጠሩ የመከላከያ አባላት ላይ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ቀደም ሲል ያስታወቀ ሲሆን በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በኩልም ምርመራ እየተካሔደ መሆኑ ተነግሯል።