የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት የኮሮናቫይረስ መነሾን አስመልክቶ እንዲካሔድ የሚሻውን ምርመራ በምን መልኩ ሊከውን እንደወጠነ ዝርዝር መርሃ ግብሩን እንዲያቀርብ፤ አለያ ግና ክሽፈትን እንደሚቀምስ ልብ እንዲል እየተነገረው ነው።
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንና የተወሰኑ ሚኒስትሮች የኮቪድ - 19 መነሾ አስባብና የቻይናን የመከላከል ጥረቶችን አስመልክቶ ዓለም አቀፍ ምርመራ ማካሔድ "ፍጹም ወሳኝ" ጉዳይ ነው በማለት እየተናገሩ ናቸው።
ይሁንና የምርመራው አካሔድ ምን ሊመስል እንደሚችል፣ ወይም እንደምን መካሔድ እንደሚገባውና በምርመራው ሂደት ወቅትም የአውስትራሊያ ሚና ምን እንደሚሆን የገለጹት ነገር የለም።
ይህንኑ አስመልክቶ "ይህ እንደምን ሊከወን እንደሚችል ፅንሰ ሃሳብ እንጂ ዝርዝር ንድፍ የለንም" ሲሉ በአውስትራሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር ዶናልድ ሮዝዌል ለ SBS ገልጠዋል።
አያይዘውም "ለመንግሥት ዋነኛው ተግዳሮት ውጥኑ ላይ የተወሰኑ ጭብጦችን ማያያዝና በተቻለ መጠን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፎችን መጠየቅ ነው" ብለዋል።

Staff wearing face masks outside the Royal Prince Alfred Hospital (RPA) in Camperdown, Sydney. Source: AAP
የመንግሥትን አቋም በብርቱ ደጋፊ የሆኑት የፌዴራል ሊብራል ምክር ቤት አባሉ ዴቭ ሻርማ በበኩላቸው "ሙሉዕ የሆነ መርሃ ግብር የዓለም መሪዎች ጠረጴዛዎች ላይ እናቅርብ ብንል እጅጉን ጊዜውን ያልጠበቀ ይሆናል"
"ለመነሻነት ዕሳቤውን ማንሸራሸር ያሻል፤ ወደ ዝርዝር ውስጥ ከመግባት በፊትም አገራት በማያመነቱበት መልኩ እንዲስማሙ ማድረግ አለብን" ብለዋል።

Liberal MP Dave Sharma. Source: AAP
የቻይና ቁጣ
እስካሁን ቻይና የሞሪሰን መንግሥትን የምርመራ ዕሳቤ አልተቀበለችም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪዝ ፓይን በቻይና በኩል ያለው ግልጽነት እንደሚያሳስባቸውና የምርመራው ቁልፍ አካልም ቻይና ወረርሽኙን አስመልክቶ ያላት ሚና እንደሚሆን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሪሰንም በፊናቸው "ለትችትነት የምናደርገው ሳይሆን፤ ይህን የምናደርገው ለሕብረተሰብ ጤና ስንል ነው" ብለዋል።
ይሁንና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጌንግ ሹዋንግ "በዚህ ወሳኝ ወቅት ፖለቲካን የተላበሰ ክስ መመስረት እጅጉን ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው" ሲሉ የአጸፋ ምላሽ ሰጥተዋል።
አክለውም፤
"በአውስትራሊያ ወገን ርዕዮተ ዓለማዊ ወገንተኝነትና ፖለቲካዊ ጨዋታዎችን ወደ ጎን በማድረግ፤ የአውስትራሊያ ሕዝብ ላይና ሉላዊ የሕብረተሰብ ጤና ደኅንነት ላይ እንዲያተኩሩ፣ ተጻራሪ ነገሮችን ከመከወን ይልቅ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ለትብብር፣ ቫይረሱን ለመፋለም እያበረከተ ያለውን አስተዋፆ እንዲከተሉ አሳስበናል" ሲሉ አክርረው ተናግረዋል።
በአውስትራሊያ የቻይና አምባሳደር ቼንግ ጂንግዪ የአውስትራሊያ የምርመራ አካሔድ ቻይናውያን ቱሪስቶች አውስትራሊያን በመጎብኘቱ ረገድ "ቆም ብለው እንዲያስቡ" ሊያደርጋቸው እንደሚችል አመላክተዋል።

Chinese Foreign Ministry spokesman Geng Shuang. Source: AAP
አያይዘውም፤
"ምናልባትም ሰዎች 'ለምን የአውስትራሊያን ወይን እንጠጣለን? የከብት ሥጋዎቿንም እንበላለን?'" ሊያሰኛቸው ይችላል በማለት ቻይና በአውስትራሊያ ላይ ልታሳድር የምትችለውን ምጣኔ ሃብታዊ ተፅዕኖዎች በአግቦ ጠቁመዋል።