የዓባይ ጉዳይ በዘመነ ነገሥታቱ
በዘመነ ምኒልክ ፈረንሳይ እንግሊዝን ከግብፅ ለማስወጣት ጣና ሐይቅን አቻ የሌለው መሣሪያዋ አድርጋ መረጠች። ንጉሠ ነገሥቱ ጣና ሐይቅ ላይ ግድብ እንዲገነቡ አበረታታች። ከናፖሊዮን እጅ ወጥታ ንግሥት ቪክቶሪያ ቅኝ ውስጥ የገባችውን የግብፅን ፖለቲካ በሾርኒ ለመቆጣጠር ዳዳች።
ፈረንሳይ ስትራቴጂያዊ ዕሳቤዋን ዕውን ለማድረግም የጂቡቲ - አዲስ አበባ የባቡር መንገድ ዝርጋታን እነሆኝ አለች። ከጣሊያን ተፃርራም ከኢትዮጵያ ጋር ወግና ቆመች። ወዳጃዊ ተፅዕኖዋንም በምኒልክ ቤተ መንግሥት ላይ ለማሳረፍ ጣረች።
ምንም እንኳ ዘግይታም ቢሆን፤ የጣና ፕሮጄክትን ብርቱ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ልብ ያለችው እንግሊዝ በሜይ 1902 የምኒልክን ሞገስ በማግኘቷ የጣና ፕሮጄክት እስከ ንጉሠ ነገሥቱ ሕልፈተ ሕይወት ተራዘመ።
በሌላ በኩል ግና ጣና ላይ ግድብ የመገንባቱ ዕሳቤ የግብፅንና የሱዳንን ቀልብ ሳበ። በግብፅ ዓይን በበጋ ፍሰቱ የሚቀንሰውን የዓባይን ወንዝ ጉድለት ለማካካስ፤ በሱዳን በኩል የጥጥ እርሻዋን በመስኖ እንደልብ ለማጠጣት።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግና የሁለቱን አገራት ዕሳቤ በቀን ሕልምነት ፈረጀው። ተዳፈነ።
ጥቂት ቆይቶም አንደኛው የዓለም ጦርነት በተነሳ በዓመቱ - በ1915 የጣና ግድብ ፕሮጄክት ትልም አሰልሶ አንሰራራ። የኢትዮጵያ፥ ግብፅና ሱዳን የጋራ ኮሚሽን ቆሞ ሐይቁን ጎበኘ።
ሲልም፤ በ1924 ራስ ተፈሪ መኮንን ለንደንን ሲጎበኙ የጣና ግድብ ፕሮጄክት በእንግሊዝ በኩል ተነሳ። በኢትዮጵያ በኩል ግድቡ የሚሠራ ከሆነ ‘ግድቡን የምትሠራው ኢትዮጵያ እንጂ ሌላ ማንም አይሆንም’ የሚል ቁርጥ ምላሽ ተሰጠ።
ይሁን’ጂ እንግሊዝና ጣልያን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጀርባ ተሻርከው ተፈሪ ላይ ጫና በማሳደር የግድቡን ሥራ ለመከወን ተስማሙ። አርፍደውም ቢሆን በወርሃ ጁን 1926 ራስ ተፈሪ የሁለቱን አገራት ስምምነት ደረሱበት። እንግሊዝና ጣልያን ያለ ኢትዮጵያ ዕውቅናና ፈቃድ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚቀናቀን ነበርና ጉዳዩን ለሊግ ኦፍ ኔሽንስ አቀረቡ። ሁለቱ አገራትም እጃቸውን እንደሚሰበስቡ ገለጡ።
ራስ ተፈሪ የመረረ ቅሬታቸውን ለእንግሊዙ ሚኒስትር በፅሑፍ ሲያስታውቁ “ከቶውንም የእንግሊዝ መንግሥት በኛ ሐይቅ ከሌላ መንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ ይደርሳል ብለን ጠርጥረን አልነበረም” አሉ።
የጣና ግድብ ፕሮጄክት ጉዳይ ውስጣቸው ዘልቆ የገባው ራስ ተፈሪ፤ በ1927 በወኪላቸው ዶ/ር ዋርኔት ማርቲን አማካይነት በኒውዮርክ የጄ.ጂ ዋይት ምሕንድስና ኮርፖሬሽን በኩል የግድብ ሥራ ወጪውን አስተመኑ። ወጪውም $20,000,000 እንደሚደርስ ተነገራቸው። ተከታታይ ጥናቶችም ከ1929 – 1935 በአሜሪካ መሐንዲሶች ተካሄዱ። በሌላ በኩል ግብፅ በ1933 እና በ1935 አከታትላ 50,000 ፓውንድስ ለግድቡ ማሠሪያ በማዋጣት ባለ አክሲዮን ለመሆን ጣረች። ኢትዮጵያ አሌ አለች።
የጣና ግድብ ጉዳይ በእንጥልጥል እንዳለም የቀዳማዊ አፄ ኃይሌ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የመጨረሻው የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት ሆኖ ከሰመ። ኢትዮጵያ የሪፐብሊክ ሥርዓትን በወታደራዊው መንግሥት አቆመች።
የዓባይ ጉዳይ በዘመነ ሪፐብሊካኖች
ከመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በትረ ሥልጣኑን የተረከበው የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ የሥርዓተ መንግሥቱን የወደፊት የጉዞ አቅጣጫ ለማሳወቅና ዓለም አቀፍ ወዳጅነትን ለማፍራት አንድ የልዑካን ቡድን አቆመ። የሚመራውም በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ ሚካኤል እምሩ ነበር። ምንም እንኳ የልዑካኑ ቡድን አንደኛው ተልዕኮ ወዳጅነትን ማፍራት ቢሆንም በዓባይ ሳቢያ ቁርሾ ላላቸው የአረብ አገራት ግልፅ መልዕክቱ የነበረው “ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃችሁን ካልሰበሰባችሁ ከእሥራኤል ጋር ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነታችንን ዳግም እንመሠርታለን። ሱዳንም ካልታቀበች ለደቡብ ሱዳን ነፃነት ታጋዮች ሙሉ ድጋፍ እናደርጋለን” የሚል ነበር።
ደርግ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) እንዳቆመ ፕሬዚደንት መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ ኢትዮጵያ በገጠማት ድርቅ ሳቢያ ለረሃብና ጉስቁልና የተዳረጉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የአንድ ሚሊየን ሔክታር የጣና በለስ የሠፈራና ልማት ፕሮጄክትን ወጠኑ። ከምኒልክ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ በጣና ሐይቅ ግድብ ሥራ ላይ ዓይኑን የጣለው የጣሊያን መንግሥት ፈጥኖ ከ300 ሚሊየን ሊሬ በላይ በእርዳታና በብድር እነሆኝ ሲል እጁን ዘረጋ።
እንደተወጠነው በሚሊየንም ባይሆን በመቶ ሺህዎች በሚቆጠር ሔክታር ላይ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍለ አገራት የሠፈሩት የድርቅ ተጎጂዎች ከተቋቋሚነት ለምርት ተረፈ ፈሰስ አቅራቢነት በቁ። ከቶውንም የምርት በረከታቸው ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ማዕድነት ለመትረፍ በቃ። ጣና በለስ ግና በቀለብ አምራችና አቅራቢነት ተወስና መቅረት አልወደደችም። አልፋ - ተርፋ አገር አቀፍ የመብራት ኃይል አቅራቢ ለመሆን ተነሳች። ግብፅና ሱዳን ግና ግንባራቸውን ቋጥረው ‘እንዴት ሆኖ?’ ብለው አፈፍ ብለው ተነሱ።
ሁለቱም አገራት የኢሕዲሪ መንግሥት ተቀናቃኞችን ከቢሮ ከፈታና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አልፈው በቀጥታና በተዘዋዋሪ የወታደራዊ ድጋፍ ችሮታቸውን አጠነከሩ። የግብፁ ፕሬዚደንት ሆስኒ ሙባረክ “የግብፃውያን ሕይወትና ብሔራዊ ደኅንነት ከዓባይ ጋር የተያያዘ እንደሆነ” አስታወቁ።
ኢትዮጵያ ግና በባለቤትነትና አይበገሬነት መንፈስ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ሥራ ጅምሯን ቀጠለች። እምብዛም ሳይቆይ በወርኃ ሜይ 1991 የኢሕዲሪ መንግሥት በተፃራሪው ኢሕአዴግ በአመፅ ተናደ። የመንግሥቱ ኃይለማርያም የኢሕዲሪ መንግሥት በመለስ ዜናዊ የኢሕአዴግ መንግሥት ተተካ። የግድብ ሥራው ንብረቶች በጠራራ ፀሐይ ተዘርፈው ተወሰዱ። ጣና በለስ ሩቅ ኣሳቢ ቅርብ አዳሪ ሆና የኤሌክትሪክ ኃይል ፕሮጄክቷ ከሰመ።
ሆኖም፤ መለስ ዜናዊ ለ20 ዓመታት ኢትዮጵያን በኢፌዴሪ ስም ከገዙ በኋላ ኤፕሪል 2011 በአፍሪካ ግዙፍ የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ የሚሆነውን የታላቁን ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቤንሻጉልና ጉምዝ አስተዳደር ከሱዳን ድንበር 50 ኪሎ ሜትሮች ፈቅ ብሎ አስጀመሩ። የ$4.8 ቢሊየን የግንባታ ወጪ የሚጠይቀው ግድብ በዕቅዱ መሠረት ግብር ላይ ከዋለ እስከ 74 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትሮች ውሃ እንደሚይዝና 6,450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመንጭ ተነገረ።
አቶ መለስ፤ ከሕዳሴ ግድብ ትሩፋቶች ተጠቃሚዎቹ የጎረቤት አገራት ቢሆኑም በተለይም የታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገራት ግብፅና ሱዳን እንደሚሆኑ ገለጡ። ይሁን’ጂ ከዕሳቤው እስከ ግንባታው ጅመራና ሂደቱ ከእሳቸው ቀድመው እንደነበሩት መሪዎች ሁሉ ከግብፅና ሱዳን ብርቱ ተቃውሞ ገጠማቸው። የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚደንት ሙሐመድ ሙርሲ ክተት ሠራዊት ባይሉም፤ ተለምዷዊ በሆነው የግብፅ የጦር ሰበቃ አዘል ንግግር “የግብፅ የውኃ ደኅንነት በጭራሽ አይደፈርም፤ ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” ሲሉ ዛቻ ለበስ ተቃውሟቸውን በአደባባይ አሰሙ።
የግብፅና ሱዳን የተቃውሞ ምንጮች ኢትዮጵያን ያላካተቱት የ1929 እና 1959 የዓባይ ተፋሰስ ውሎች ናቸው። የ1929ኙ ውል የተካሄደው በእንግሊዝና ግብፅ መካከል ሲሆን እንግሊዝን ጣልቃ ያስገባት ‘የቅኝ ተገዢዎቿ የዓባይ ተፋሰስ ጥቅም አስከባሪ’ የሚል አስባብ ነው። በ1929ኙ ውል መሠረት፤ ከዓመታዊ የዓባይ ፍሰት ግብፅ 48 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ሱዳን 4 ቢሊየን እንድታገኝ ይደነግጋል። ዐልፎም፤ ግብፅ በዓባይ ወንዝ ላይ በሚደረጉ ማናቸውም ግንባታዎች ወይም የዓባይ ወንዝን ፍሰት በሚቀንሱ ገባር ተፋሰሶች ላይ በሚደረጉ ማናቸውም ክንውኖች ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቶችን ሁሉ አክሎ ይሰጣል።
በ1959 በግብፅና ነፃ በወጣችው ሱዳን መካከል የተደረገው የሁለትዯሽ ውል ደግሞ ከቶውንም ግብፅ በ1929ኙ ውል ሰፍሮ ከነበረው 48 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትሮች ወደ 55.5 ኪዩቢክ ሜትሮች ከፍ ሲል፤ የሱዳን ከ4 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትሮች ወደ 18.5 ኪዩቢክ ሜትሮች አሻቅቧል። አክሎም እንደ 1929ኙ ሁሉ የ84 ፐርሰንት የዓባይ ተፋሰስ ባለቤቷን ኢትዮጵያን ጨምሮ ማናቸውም አገራት የዓባይን ፍሰት ሊያስቀንስ ይችላል ተብለው ከሚታሰቡ ክንውኖች እንዲቆጠቡ ይደነግጋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከቀድሞ የአማፂነት ዘመን ሽርካዎቻቸው ግብፅና ሱዳን ብርቱ ተቃውሞዎች ቢገጥማቸውም፤ እምቢኝ ብለው እስከ 2012 ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ገፍተው አስቀጥለዋል።
በአቶ መለስ መንበር የተተኩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የሕዳሴ ግድብ ሌሎች አገራትን እንደማይጎዳ መተማመኛ ለመስጠት በሚል ዕሳቤ በ2015 የ‘ካርቱም ስምምነት’ ከግብፅና ሱዳን መሪዎች ጋር ፊርማቸውን አኑረዋል። ያም ለዛሬው የዋሽንግተን ዲሲ ድርድር አስባብ ሆኗል።
ከካርቱም እስከ ዋሺንግተን ዲሲ
የማርች 2015ቱ ‘የመርሆች ስምምነት በታላቁ የኢትዯጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት’ ወይም በግብፅና ሱዳን ተመራጭ አጠራር ‘የዓባይ ስምምነት’ አዝጋሚም ቢሆን መዘዝ አዘል ሆኗል። ግብፅና ሱዳን ሆን ብለው ‘የዓባይ ስምምነት’ በሚል መጥራቱን የሚሹትን የአገራቱ መሪዎች ፊርማቸውን ያኖሩበት የስምምነት ሰነድ “Agreement on Declaration of Principles between The Arab Republic of Egypt, The Federal Democratic Republic of Ethiopia And The Republic of the Sudan On The Grand Ethiopian Renaissance Dam Project (GERDP)” ማለቱን ስተውት ሳይሆን፤ በሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት ላይ ብቻ የማይረጉ መሆናቸውን የሚያሳስብ ስነልቦናዊ ተፅዕኖ አሳዳሪና አጀንዳ ቀረፃ አድርጎ ግምት ማሳደር ይቻላል።
ባለ 10 አንቀፁ የማርች 23, 2015 የካርቱም ፈራሚዎች፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ (2012 - 2018)፥ የግብፅ ፕሬዚደንት አብደል ፈታህ አል_ሲሲ (2014 - እስካሁን) እና የሱዳን ፕሬዚደንት ኦማር አል_በሽር (1989 - 2019) ናቸው።
የመርሆዎች መግለጫው አንቀፅ 10 ሶስቱ አገራት በአተረጓጎም ወይም አተገባበር ላይ ያሏቸውን የአቋም ልዩነቶቻቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ፤ ዕልባት ማበጀት ካልሆነላቸውም በምክክር፥ በድርድር ወይም በሽምጋይ፤ አለያም በርዕሳነ መንግሥታት ወይም መስተዳድራት በኩል ብልሃት እንዲያፈላልጉ በማበረታት ይቋጫል።
X. Principle of Peaceful Settlement of Disputes
• The Three countries will settle disputes, arising out of the interpretation or implementation of this agreement, amicably through consultation or negotiation in accordance with the principle of good faith. If the Parties are unable to resolve the dispute through consultation or negotiation, they may jointly request for conciliation, mediation or refer the matter for the consideration of the Heads of State/Head of Government.
የ2015ቱን የመርሆዎች ስምምነት ተከትሎ ሶስቱ ፈራሚ አገራት ተከታታይ ድርድሮችን አካሄዱ። ከሁሉም በላይ ግብፅ ያሻችውን ባለማግኘቷ ዩናይትድ ስቴትስን በሸምጋይነት እንድትዳኝ ተማፀነች።
ሆኖም፤ ኤፕሪል 2, 2018 ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያምን የተኩት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ፈጣን ምላሽ ‘እምቢታ’ ሆነ። ትንሽ ቆይቶ ግና በጫናም ይሁን በድለላ ተሳታፊነቱን ገለጠ። በውጭና የውኃ ሚኒስትራት የሚመራ የቴክኒክና የሕግ ልዑካን ቡድን አባላትን አሰናድቶም ወደ አገረ አሜሪካ ላከ።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የኢትዮጵያ፥ ግብፅና ሱዳንን የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትሮችን ተቀብለው አነጋገሩ።
የዩናይትድ ስቴትስ በጅሮንድና የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት በታዛቢነት በተገኙበት የሶስቱ አገራት የውጭ ጉዳይና የውኃ ሚኒስትራት፥ የሕግና የውኃ ቴክኒክ ባለሙያዎች የመጀመሪያ ድርድራቸውን ኖቬምበር 06, 2019 በዋሽንግተ ዲሲ ጀመሩ። የድርድሩ ዋነኛ ትኩረትም፤

US President Donald Trump with top representatives from Ethiopia, Egypt, and Sudan on the Grand Ethiopian Renaissance Dam Source: Courtesy of Trump's Twitter account
- በድርቅ
- በዓመታት የተራዘመ ድርቅና
- በተራዘመ ድርቅ ዓመታት አነስተኛ የወንዝ ፍሰት ወቅት የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ላይ ሆነ።
ሶስቱ ተደራዳሪ አገራት አራት ተከታታይ ድርድሮቻቸውን በዋሽንግተን ቢያካሂዱም ከስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም። ልዩነቶች በተለይም በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ጎልተውና ሰፍተው ወጡ።
በኢትዮጵያ ወገን “የዓባይ ወንዝ በግድቡ ሥፍራ በሚኖረው የፍሰት መጠን ከ4 - 7 ዓመታት በሚወስድ የሙሌት ደረጃ ግድቡ እንዲሞላ፤ የግድቡ ሙሌት ከተጠናቀቀ በኋላ ድርቅ ቢከሰት የማቃለያ እርምጃ እንዲወሰድ” የሚሉ የመስማሚያ ሃሳቦች ቀረቡ።
በግብፅ በኩል “ኢትዮጵያ ከ12 - 21 ዓመታት ጊዜያት ውስጥ የሕዳሴ ግድብን እንድትሞላ፤ ከመጀመሪያው የውኃ ሙሌት በኋላ ለግብፅ የውኃ ሙሌት ጉድለት ማካካሻ እንድትሰጥ” የሚሉ የመደራደሪያ ሳይሆን “ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብቷ” መሆኑን የሚያሳውቅ የግዴታ አፈፃፀም አቋሟን ይዛ ፀናች።
ይህ ዓባይን አስመልክቶ ግብፅ “ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት” የሚለውን አጀንዳ የማፅኛና ብሔራዊ ስሜትን የመቀስቀሻ ዘዬ በመጠቀም በግብፃውያን አንደበት ለመሰልጠን የበቃው የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሙሐመድ ማሕሙድ (27 ጁን 1928 – 4 ኦክቶበር 1929) ለወቅቱ የእንግሊዝ አምባሳደር ሎርድ ሎይድ ዓባይን አስመልክተው በፃፉት ደብዳቤ ላይ “የዓባይ ወንዝ የግብፅ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብቶች ነው” ሲሉ ከፃፉና በምዕራባውያኑ ጋዜጦች ተደጋግሞ ለሕትመት መብቃት ከጀመረ ወዲህ ነው።
እርግጥ ነው፤ ተመክሮበትም ይሁን በአጋጣሚ በኢትዮጵያ ወገን ዓባይን ለ “ልማት፥ ዕድገትና ብልፅግና መጠቀም የኢትዮጵያ መብት ነው” ተብሎ ሲነገር ይደመጣል። ብሔራዊ ስሜትን አነሳሽነቱ የለዘበም ቢሆን፤ ለግንዛቤ ማስጨበጫነት ማገዙ ግና አሌ የሚባል አይደለም።
የዐቢይ አስተዳደር በጭብጥ ወይም መሪ ቃል (theme) አቀራርፁ ላይ ላላ ቢልም፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበሩ ረገድ ግና በልዩነት አቋሙ ፀንቶ ቆመ። ሆኖም፤ ተደራዳሪዎቹ ግብፅና ሱዳን፤ ታዛቢዎቹ ዩናይትድ ስቴትስና የዓለም ባንክ ፌብሪዋሪ 27 - 28, 2020 ኢትዮጵያ በታደመችበት የድርድሩ ዕልባት ማበጃና የፊርማ ሥነ ሥርዓት ማካሄጃ ብለው ፅኑ ተስፋ አሳደሩ።
በመሃሉ ዩናይትድ ስቴትስ ከታዛቢነቷ ባለፈ ለሶስቱ ተደራዳሪ አገራት የውኃ ሚኒስትራት የስምምነት ረቂቅ ሰነድ ላከች። ግብፅና ሱዳን አዎንታዊ ምላሻቸውን አስታወቁ። ኢትዮጵያ በውጭ ጉዳይ ሚንኒስትሯ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አማካይነት እንደታሰበው ዋሽንግተን ዲሲ ከፌብሪዋሪ 27 - 28, 2020 ለመገኘት የጀመረኩትን የባለሙያዎች ምክክር ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ‘የይራዘምልኝ’ የጊዜ ጥያቄ በዲፕሎማሲያዊ ቋንቋ አቀረበች።
ዩናይትድ ስቴትስ ብርቱ የአፀፋ ምላሽ ለኢትዮጵያ ላከች። ሱዳንና ግብፅም ተቆጥተው ተነሱ። ከቶውንም ግብፅ የሕዳሴ ግድብን የአረብ - ኢትዮጵያ ጉዳይ አድርጋ ለአረብ ሊግ አቀረበች። ሰሞኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ የአረብ አገራቱ መሪዎች ዘንድ የፕሬዚደንት አል ሲሲን ደብዳቤዎች ይዘው እየቀረቡ ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ናቸው።
የዐቢይ አስተዳደርም ከ 5 - 10 ዓመታት የሚያገለግለውን አዲስ ስትራቴጂ ለመንደፍ ከውሳኔ ላይ ደርሷል። የውኃ ቴክኒክና የሕግ ቡድናቱን ለማጠናከር እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል። የመጀመሪያ የሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌቱን ዕውን ለማድረግ ወርኃ ጁላይን እየጠበቀ ይገኛል።
ሂደቱ እንደ ዓባይ ፍሰት ዝግ ያለ ግና ብርቱ ሆኖ ይቀጥላል…