ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ዛሬ ማለዳ ላይ የSBS አማርኛ ፕሮግራምን አካትቶ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ትናንት ይፋ የሆነውን የፌዴራል በጀት 2020/21 አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ሞሪሰን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ የመላው ዓለም ምጣኔ ሃብት ለድቅቀት እንደበቃ ጠቁመው የአውስትራሊያ ጠቅላላ ምርት ዕድገትም በሰባት ፐርሰንት ማሽቆልቆሉን ገልጠዋል። ሆኖም የአውስትራሊያ ምጣኔ ሃብት ከሌሎች በርካታ ያደጉ አገራት ጋር ሲነጻጸር በተሻለ ሁኔት ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
ከምጣኔ ሃብታዊ ድቅቀቱ አገግሞ ለመውጣት በጀቱ ያተኮረባቸውን ሶስት ዋነኛ ጉዳዮች ሲያነሱ፤
- አውስትራሊያን ገጥመዋት ያሉት ምጣኔ ሃብታዊ ተግዳሮች
- የምጣኔ ሃብት ማገገሚያ ፕላን
- የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ዕቅዶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በወረርሽኙ ሳቢያ ባለፉት ወራት ተከልተው ወይም ወደ ዜሮ ሰዓታት ወርደው የነበሩ 760 ሺህ ሥራዎች ዳግም መመለሳቸው ያስደሰታቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
አውስትራሊያ በመድብለ ባሕል ፖሊሲ ትግበራዋ ስኬታማ መሆኑን በማንሳትም መጤዎች ጠያቂዎች ሳይሆኑ ታትሪ ሠራተኞችና ሥራ ፈጣሪዎች መሆኗቸውን አስገንዝበዋል። አያይዘውም፤ "ሁላችንም በአንድነት ስንቆም አገራችን ይበልጡን ለስኬትና ዕድገት ትበቃለች" በማለት በመጤዎችና በቀድሞ ነዋሪዎች መካከል ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በእኩል ዜግነት መንፈስ በአውስትራሊያዊነታቸው እንዲቆሙና ለጋራ ዕድገት የዜግነት አስተዋፅዖዎቻቸውን እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
በማከልም፤ የእንግሊዝኛ ቋንቋን ጠቀሜታ አስመልክተው ሲናገሩ "እንግሊዝኛ ቋንቋ ለማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ተካታችነት ብርቱ መሳሪያ ነው - እንግሊዝኛ ቋንቋ ፓስፖርት ነው" ብለዋል።
የዓለም አቀፍ ድንበር ከፈታን በተመለከተም በቅድሚያ ከኒውዝላንድ ጋር ቀጥሎም ከኮሪያ፣ ጃፓንና ሲንጋፖር ጋር ሁኔታዎች በፈቀዱ መልክ ዓለም አቀፍ ድንበሮችን ለመክፈት ዕቅድ መኖሩን ጠቁመዋል። እንዲሁም በሚቀጥለው ዓመት ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ወደ አውስትራሊያ የሚመጡበት መንገዶች እየተመቻቹ እንደሆነና ሆኖም በጥድፊያ የሚከናወን አለመሆኑን ገልጠዋል።