ቻይና በአራት የአውስትራሊያ የእርድ ሥጋ አቅራቢ ድርጅቶች ላይ የጣለችውን ዕገዳ አስመልክቶ በቻይና ሚዲያ በኩል ለአውስትራሊያ "የማንቂያ ደወል" ስለመሆኑ እየተስተጋባ ነው።
የአውስትራሊያ ንግድ ሚኒስትር ሳይመን በርሚንግሃም ለእንወያይ ጥያቄያቸው በቻይና በኩል እስከ ዛሬ ረቡዕ ምላሽ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል።
"ለምን ምላሽ እንዳልሰጡን ይህ ነው ለማለት አልችልም። በእኔ በኩል በሬ ክፍት ነው፤ ተግናኝቶ ለመነጋገር ዝግጁና ፈቃደኛ ነኝ"
"የቻይና የንግድ ሚኒስትርን ለውይይት ጠይቄያለሁ፤ እስካሁን ምንም ምላሽ የለም። ይሁንና የግንኙነት መስመራችንን ክፍት አድርገን እንቆያለን" ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻን አስመልክቶ ምርምራ ይካሄድ ብለው ሉላዊ ዘመቻ ከጀመሩ ወዲህ ለውጥረት ተዳርጓል።

Trade Minister Simon Birmingham. Source: AAP
ቻይና በአራቱ የሥጋ አቅራቢዎች ላይ የጣለችው ዕገዳ የአውስትራሊያን 35 ፐርሰንት የከብት ሥጋ የውጭ አቅርቦት የያዘ ነው።
አሥራ ስምንት ፐርሰንት የአውስትራሊያ የከብት ሥጋ የውጭ አቅርቦት ምርት የሚላከው ወደ ቻይና ሲሆን፤ ለአውስትራሊያ የሚያስገኘው ገቢም በዓመት $3 ቢሊየን ነው።
ቀደም ሲልም ቻይና ወደ አገሯ በሚላከው የአውስትራሊያ የገብስ የውጭ አቅርቦት ላይ የ80 ፐርሰንት ታሪፍ ጥላለች።
ይሁንና የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዛዎ ሊያን ማክሰኛ ምሽት የቻይና እርምጃ ከአውስትራሊያ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ድጋፍ ጋር ተያያዥነት እንደሌለው ገልጠዋል።
ለዕገዳው እርምጃ አስባብ የሆነው የጉምሩክ መኮንንኖች የጥራት ቁጥጥር ሲያካሂዱ የተወሰኑ የአውስትራሊያ የከብት ሥጋ አቅራቢዎች "ተደጋጋሚ ጥሰቶችን" ፈጽመው በመገኘታቸው እንደሁ ጠቁመዋል።
አያይዘውም፤
"በቻይና በኩል በአውስትራሊያ ወገን ችግሩን አስመልክቶ ሙሉዕ ምርመራ ተካሂዶ ጉዳዩ ዕልባት እንዲያገኝ ተጠይቋል" ብለዋል።
የአውስትራሊያ የሥጋ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት የዕገዳውን ምክንያት ከምርት ዝርዝር መግለጫ ጉዳይ ጋር አያይዞታል።

Chinese Foreign Ministry spokesman Zhao Lijian attends a press conference in Beijing. Source: Kydpl Kyodo
ሆኖም የናሽናልስ ፓርቲ ምክር ቤት አባል ጆርጅ ክሪስቲንሰን ግና የቻይናን ድርጊት ከጠበኝነትና የኃይል ጫና አሳዳሪነት ጋር አያይዘው ሲናገሩ፤
"ቻይና በአሁኑ ወቅት እያደረገች ያለችው በጣሙን አሳስቦኛል። ዋነኛ ኢንዱስትሪዎቻችንን እየጎዱብን ነው። ይህ ጠበኝነትና ኃይል የተመላው የጫና ድርጊት ነው፤ ይህ እንዲህ ባለ መልኩ መቀጠል የለበትም" ሲሉ ለ SBS News ተናግረዋል።

Nationals MP George Christensen Source: SBS
የብሔራዊ ገበሬዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ፊዮና ሲምሰን በበኩላቸው የውጭ አቅርቦቱ መስተጓጎል አሳስቢ መሆኑን ገልጠዋል።
አክለውም፤
"በአውስትራሊያና ቻይና መካከል ያለው ግንኙነት በጣሙን ጠቃሚ መሆኑንና አልፎ አልፎም አንዳንድ ነገሮች እንደሚከሰቱ እንገነዘባለን"
"ሲከሰቱም ሁለቱ ወገኖች መከባበር በተመላበት ሁነት በተቻለ ፍጥነት ለሁለቱም አርኪ በሆነ መንገድ እክሉን መክላት አለባቸው" ሲሉ ምክረ ሃሳባቸውን አክለው ተናግረዋል።
የሌበር የግብርና ቃል አቀባይ ጆ ፊትዝጊበን በፊናቸው ለንግድ መስተጓጎሉ ክስተት የፌዴራል መንግሥቱ የራሱ ድርሻ እንዳለው ሲያመላክቱ፤

NFF President Fiona Simson Source: AAP
"መንግሥት ዋነኛ ከሆነች የንግድ ሽርካችን ጋር ያለውን ግንኙነት ሲያዛንፍ እንዲህ ያሉ የምጣኔ ሃብት መዘዞችን እንደሚያስከትል መጠበቅ ይቻላል" ብለዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ በካንብራ የቤጂንግ አምባሳደር ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በምርመራ ጥሪያቸው ከቀጠሉ ቻይናውያን የአውስትራሊያን የክብት ሥጋና ገብስን መሸመቱ ላይ ቆም ብለው ሊያስቡ ይችሉ ይሆናል ማለታቸው ይታወሳል።

Labor's spokesperson for agriculture Joel Fitzgibbon Source: SBS
የንግድ ሚኒስትር ሳይመን በርሚንግሃም የአውስትራሊያ ምርመራ ይደረግ ግፊት ከከብት ሥጋና ገብስ የውጭ ምርት አቅርቦት ጋር እንደማይያያዝ ተስፋቸውን ገልጠዋል።
የቻይና ግሎባል ታይምስ በበኩሉ፤ የቻይና እርምጃ አውስትራሊያን በምጣኔ ሃብት ለመቅጣት ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይገባ ጠቁሞ "ቻይና ለአውስትራሊያ መጠነ ሰፊ የውጭ ምርት አቅርቦቶች ብቸኛ ምርጫ ስትሆን፤ አውስትራሊያ ግና ለቻይና ብቸኛ አማራጭ አይደለችም" ብሏል።