በትግራይ ክፍለ አገር ቶጎጋ ከተማ ማክሰኞ ዕለት በደረሰ አንድ የአየር ጥቃት 43 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን አንድ የሕክምና ኃላፊ ለሮይተርስ የገለጠ ሲሆን ነዋሪዎችም በሰሜናዊ መቀሌ በኩልም አዲስ ውጊያ መቀስቀሱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ሁነቱን አስመልክቶ ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ አልሰጡም። ኮሎኔሉ የአየር ጥቃት የተለመደ ወታደራዊ ታክቲክ መሆኑንና መንግሥት ሰላማዊ ሰዎችን ዒላማው እንደማያደርግ ገልጠዋል።
ባላቸውና የሁለት ዓመት ሴት ልጃቸው እንደቆሰሉባቸው የተናገሩት አንዲት ሴት ቦምቡ አንድ የገበያ አካባቢ ላይ ከቀትር በኋላ 7 ሰዓት (1pm) መውደቁን አመልክተዋል።
አያይዘውም "አውሮፕላኑን አላየንም፤ ድምጹን ግን ሰምተናል" ሲሉ ረቡዕ ዕለት ለሮይተርስ ተናግረዋል። በማከልም "በፍንዳታው ወቅት ሁሉም ሰው እግሬ አውጪኝ አለ። ጥቂት ቆይተን በመመለስ ቁስለኞችን ለማንሳት ሞክረናል" ብለዋል።
ሴቲቱ ገበያው በቤተሰቦች የተሞላ እንደነበርና በአካባቢው አንድም ታጣቂ ኃይሎችን ያለማየታቸውን ገልጠዋል። "ብዙ፣ በርካታ" ሰዎች ተገድለዋል ሲሉም አክለዋል።
ሆኖም የሴቲቱን አባባል ሮይተርስ በገለለተኛነት ማረጋገጥ አልቻለም። ሴቲቱና ሌሎች የመረጃ ምንጮች በቀል እንዳይደርስባቸው ካላቸው ፍርሃት ማንነታቸው እንዳይገለጥ ጠይቀዋል።
የሕክምና ባለስልጣኑ 43 ያህል ሕይወቶች መቀጠፋቸውን የዓይን እማኞችንና የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎችን ዋቤ ነቅሰው ገልጠዋል።
ክስተቱን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቃል አቀባይና የመንግሥት የትግራይ ግብረ ኃይል ኃላፊ በኩል ለቀረበላቸው የማብራሪያ ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።
በአየር ጥቃቱ ሳቢያ ያለፉ ሕይወቶችን አስመልክቶ የቀረቡት ሪፖርቶች የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በእጅጉ ያሳሰባቸው ሲሆን፤ የተመድ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ ኒው ዮርክ ውስጥ ለሪፖርተሮች በሰጡት መግለጫ ሁለቱም በግጭት ላይ ያሉ ወገኖች ለዓለም አቀፍ ሕግ ተገዢ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።

Injured residents of Togoga, a village about 20km west of Mekele, wait at the Ayder referral hospital in Mekele, Ethiopia, on 23 June, 2021. Source: AFP via Getty Images
"ወደ አካባቢው ዘልቀን ሁኔታዎችን ለመገምገምና እንደምን እርዳታ ማድረግ እንደምንችል ለመመልከት ፈቃድ የጠየቅን ቢሆንም እስካሁን ያን ማድረግ አልቻልንም። በዚያ አካባቢ ያለው ሁኔታ በጣም በጣም ተለዋዋጭ ነው" ሲሉም ገልጠዋል።
የተመድ ረድኤት ገዲብ ባለስልጣን ራሜሽ ራጃሲንግሃም የኢትዮጵያ ባለስልጣን ጥቃቱን አስመልክቶ "ፈጣንና ውጤታማ ምርመራ" እንዲያካሂድ ጠይቀዋል።
የአየር ጥቃቱ ዜና የመጣው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ኃላፊዎች ከ10 ክልሎች በሰባቱ የአገር አቀፍና የክልል ፓርላማ ምርጫዎችን ድምጾች እየቆጠሩ ባሉበት ሳምንት ነው።
ጦሩ ከሕወሓት ታማኞች ጋር ከወርኃ ኖቬምበር ጀምሮ በሚፋለምባት ትግራይ ውስጥ ምርጫ አልተካሔደም።
ነዋሪዎች የሕወሓት ታጣቂዎች በሰሜናዊ መቀሌ ባሉ በርካታ አነስተኛ ከተሞች ባለፉት ሶስት ቀናት ገብተው እንደነበረና ካንደኛው አንስተኛ ከተማ በሰዓታት ውስጥ ለቅቀው መውጣታቸውንም ተናግረዋል።
'አምቡላንስ ተከልክሏል'
በቶጎጋ የሕክምና እገዛ ላይ የነበሩ አንድ ኃላፊና ሁለት የጤና ሠራተኞች ረቡዕ ዕለት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከመቀሌ ወደ ከተማዪቱ የሚያስገባውን አውራ ጎዳና ዘግተው አምቡላንሶች አደጋው ወደ ደረሰበት ሥፍራ እንዳይገቡ ማድረጋቸውን ለሮይተርስ ጠቁመዋል።
የጤና ኃላፊው ሁለት አምቡላንሶች ከጀርባ ባለ መንገድ ማክሰኞ ረፋዱ ላይ ወደ ከተማይቱ መዝለቃቸውንና ሆኖም በቂ የሕክምና ቁሳቁሶች የሌላቸው እንደነበሩና ሥፍራውንም ለቅቀው መውጣት እንዳልቻሉ ገልጠዋል።
የጤና ኃላፊው አክለውም የሕክምና ቡድኖቹ አደጋው በደረሰበት ሥፍራ 40 ያህል ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎችን እንደቆጠሩ፣ ሶስት ሰዎች ለሊቱን ሕይወታቸው ማለፉንና 44 በፅኑዕ ቆስለው ሕክምና የሚሹ ሕመምተኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

Relatives wait for the arrival of amburances outside the Ayder referral hospital in Mekele, the capital of Tigray region, Ethiopia, on 23 June, 2021. Source: AFP via Getty Images
አንድ ሌላ የሕክምና ሠራተኛም በበኩሉ 20 ያህል የጤና ሠራተኞችና ስድስት አምቡላንሶች ማክሰኞ ዕለት ቁስለኞችን ለመታደግ ቢጥሩም አንድ የፍተሻ ጣቢያ ላይ በወታደሮች መገታታቸውን ገልጧል።
አክሎም "ወደ ቶጎጋ መሔድ እንደማንችል ነገሩን። ከአንድ ሰዓት በላይ የፍተሻ ጣቢያው ላይ ቆይተን ለመደራደር ሞከርን። ከጤና ቢሮ የተሰጠንን ደብዳቤ አሳየናቸው፤ ይሁንና ትዕዛዝ ነው አሉን" ብሏል።
ሆኖም የጦሩ ቃል አቀባይ ኮሎኔል አዳነ ሠራዊቱ አምቡላንሶችን እንዳላገደ ተናግረዋል።