"አገር የደም ዕንባ ማንባቷ እንዳይቀጥል ለሰላም የሚዘረጉ እጆች አይዛሉ” እናት ፓርቲ

*** "መሠረቱ ለሰላም ታላቅ ዋጋ ከሚሰጥ ሕዝብ አብራክ የወጣ፤ አሁን በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘውግ ተኮር፣ እጅግ ፈታኝ የሆነ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም ግድያና መፈናቀል እንዴት መፍታት አቃተን?" እናት ፓርቲ

A woman, who fled the violence in Ethiopia's Tigray region.

A woman, who fled the violence in Ethiopia's Tigray region. Source: Getty

የእናት ፓርቲ ሐምሌ 14 አገር አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ተከስተው ያሉ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ ዕልባት እንዲያገኙ ጥሪና ምክረ ሃሳቦቹን አቅርቧል። 

ፓርቲው ሰላም ወዳድነትና አክባሪነት የኢትዮጵያውያን ዕሴትነት ነቅሶ "መሠረቱ ለሰላም ታላቅ ዋጋ ከሚሰጥ ሕዝብ አብራክ የወጣ፤ አሁን በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘውግ ተኮር፣ እጅግ ፈታኝ የሆነ የእርስ በእርስ ግጭት እንዲሁም  ግድያና መፈናቀል እንዴት መፍታት አቃተን?" በማለት ለዜጎች የኅሊና መጠይቅ አቅርቧል።

ችግሮችን በማመላከት ብቻ ሳይወሰንም ለሰላማዊ መፍትሔ ይበጃሉ ያላቸውንም ምክረ ሃሳቦች አቅርቧል።

  1. 1.     ኢፌዴሪ መንግስት፡-
  • የሀገራችንን ሰሜናዊ ድንበር ለመጠበቅ በትግራይ ክልል በተመደበው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ የተፈጸመውን ዘግናኝ ተግባር ለመመከት የተወሰደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ፤ በትግራይ ክልል የሚገኘው ሕዝብም ከመከላከያ ጎን ሆኖ ያሳየው የወቅቱ ትብብር፤ መንግስት ያለውን አቅም ተጠቅሞ ለሰብዓዊ እርዳታ የሰጠው ትኩረት የሚመሰገን ሲሆን ይኸው ተጠናክሮ  መቀጠል እንደሚኖርበት እናሳስባለን፤
  •  መንግስት ተቀዳሚ ሓላፊነት እንዳለበት አካልና በታሪክ አጋጣሚ ሀገር በእጁ ላይ እንዳለች አውቆ የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል አለመረጋጋት ለዘመናት ክፉና ደጉን በአብሮነት በተሻገረው በአማራና  በትግራይ ክልል ሕዝብ መካከል የሚካሄድ ጦርነት የሚያስመስሉ ንግግሮች ለሀገራችን ታሪካዊ ስህተትን የሚያመጡ ስለሆኑ በፍጥነትና በጥንቃቄ የሀገርን ሰላም የማስጠበቅ ሓላፊነቱን አበክሮ እንዲወጣ እናት ፓርቲ በጥብቅ ያሳስባል፤
  • በውጭም ይሁን በውስጥ ጫና ባልተጠና መንገድ በሚመስል መልኩ የሚወሰኑ ውሳኔዎች መጨረሻቸው የሀገርን ሁለገብ ውድቀት ስለሚያስከትሉ እንዲታሰብባቸው፤ እንዲሁም መንግስት ትክክለኛ መረጃዎችን በተገቢው አካልና በጊዜው ለሕዝብ በማድረስ ሕዝብ በሐሰት መረጃ እንዳይደናገር እንዲያደርግ፤
  • ከወቅታዊ ችግር ጋር በተገናኘ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች በሚኖሩ ዜጎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ላይ የሚወሰደው የእስር፣ ከሥራ እገዳና የማዋከብ እርምጃ ሌላ መልክ እንዳይዝ ተገቢ የሆነ ጥንቃቄ እንዲደረግና ሕግንና ሕግን ብቻ የተከተለ እንቅስቃሴ እንዲኖር ማድረግ፤
  • ዓለም አቀፍ ጫናውን ብቃቱና ልምዱ ባላቸው ባለሙያዎች እየተመራ መቋቋም የሚያስችሉ የረጅምና የአጭር ጊዜ ስልቶች እንዲቀየሱ፤  
  • በክልሎች መካከል የሚነሱ የወሰን ግጭቶች በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኙ ለማስቻል ሁሉን አቀፍ ውይይት በማካሔድ ጎሳ ተኮር ፖለቲካውን በመሠረታዊ መልኩ ለመለወጥ የሚያስችል የሕገ መንግስት ማሻሻያ ለማድረግ ከወዲሁ እንቅስቃሴ እንዲጀመር እናሳስባለን፡፡
  1. 2.     በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ቡድን፡- 
በተደጋጋሚ ሀገር ወዳድ ሽማግሌዎች ያደረጉት የማወያየትና የማቀራረብ ሂደት እንዳይሳካ በማድረግ ብሎም በትግራይ ክልል በሚገኘው የመከላከያ ሠራዊት ላይ ግፍ በመፈጸም ታሪካዊ ስህተት መሥራታችሁን በእጅጉ የምናወግዘው ተግባር ነው፡፡ በዚሁ መነሻነት ለአሥርት ዓመታት በመከራ የኖረው የትግራይ ሕዝብ በጦርነት እንዲማገድ መደረጉ በእጅጉ ያሳዝነናል፡፡

ጣታቸው እርሳስና ደብተር መያዝ ያለበትን ሕጻናት ከክብደታቸው በላይ የሆነ መሣሪያ አሸክሞ ወደእሳት መማገድ ይቅር የማይባል ወንጀል፣ በዓለም አቀፍ ሕግም የተከለከለ በመሆኑ ከእኩይ ድርጊታችሁ እንድትታቀቡ እናሳስባለን፡፡

አሁንም ቢሆን በትግራይ ያለ ማኅበረሰባችን ከጦርነት ተላቆ በሰላም ሠርቶ እንዲገባ እንዲሁም የተፈጠሩ ችግሮችን ከተቀረው የሀገራችን ሕዝብ በተለይም ከወንድሙ የአማራ ማኅበረሰብ ጋር በመመካከርና በውይይት ለችግሮች እልባት እንዲሰጥ አሁንም በታሪክ ፊት ይቅርታን የሚያስገኝላችሁን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ በማቆም ዜጎቻችንን ከባሰ መከራና እንግልት እንድትታደጉ እናሳስባለን፡፡

  1. 3.     ለአማራ ክልላዊ መንግስት፡-
የአማራ ክልል ሕዝብ ከትግራይ ክልል ወንድም ሕዝብ በሃይማኖት፣ በታሪክና በማኅበራዊ ሕይወት ተጋምዶ ዘመናትን የተሻገረ ለመሆኑ ከማንም ያልተሰወረ ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም የተፈጠረው ችግር ቁርሾን ወልዶ ሀገራችንን ለሌላ ሰቆቃ እንዳይዳርግ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግና አሁንም በሰላም የሚፈታበትና የሁለቱም ክልል ሕዝብ በቆየው እሴቱ ችግሮችን እንዲፈታ ለማድረግ ከአሁን ቀደም ካደረጋችሁትም በላይ ለሰላም የሚዘረጋ እጃችሁ እንዳይታጠፍና የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች አሸናፊ በሚያደርግ ሰላማዊ ድርድር እንዲፈታ ለማድረግ ጥረት እንድታደርጉ እንጠይቃለን፡፡

  1. 4.     ለተከበራችሁ የትግራይና የአማራ ሕዝቦች፡-
ወቅታዊው ግጭት ለዘመናት ከቆየ ዘርፈ ብዙ ጠንካራ ግንኙነቱ በዘለለ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን ለሀገር ግንባታ ለሠራችሁት ደማቅ ታሪክ ፈፅሞ የማይመጥን ብቻ ሳይሆን ለትግራይም ይሁን ለአማራ ሕዝብ ኪሳራ እንጂ ትርፍ የማያስገኝ ነው፡፡

ሁለቱ ማኅበረሰቦች ፖለቲከኞች በቆሰቆሱት እሳት መማገድ ስለሌለባችሁ እና አንዱም አሸናፊ ሳይሆን ሁለታችሁንም ብሎም ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር ተሸናፊ የሚያደርግ የውርደት አቅጣጫ መሆኑን በመገንዘብ ከወዲሁ በሰላማዊ መንገድ ነገሩን ለመቋጨትና ግጭቱ ሕዝባዊ ቁመና እንዳይኖረው እንደ ሕዝብ ድርሻችሁ የጎላ ነው፡፡

በመሆኑም ይህን ታሪካዊ ሓላፊነት ለመወጣት የአማራና የትግራይ ሕዝብ ከመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ታሪክ እንደሚያስተምረን በመላው ዓለም የተከሰቱ ጦርነቶች ሁሉ መቋጫቸው ድርድርና ውይይት ስለሆነ ለግጭቱ ሀገር በቀል መፍቻ መንገዶች የሃይማኖት አባቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ምሑራንን፣ ወጣቶችንና ሌሎችንም በጎ ሀሳብ ያላቸውን አካላት ያካተተ ስብስብ ተቋቁሞ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያፈላልግ ስንል ጥሪያችንን በታላቅ አክብሮት እናስተላልፋለን፡፡

  1. 5.     ለብዙኃን የመገናኛ ተቋማትና ማኅበራዊ አንቂዎች፡- 
ምንም አንኳን ሙያዊ ግዴታችሁን ለመወጣት ያለ ዕረፍት እየሠራችሁ ያላችሁ የብዙኃን መገናኛ  አካላት ብትኖሩም አንዳንዶች ግን የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተጠቅማችሁ ሕዝባችንን ለሰላም፣ ለልማት፣ ለሀገር ግንባታ፣ ለአብሮነት፣ ከማትጋት ይልቅ ጦርነትን በማራገብ የተለወጠ ሀገር ያለ ይመስል የጦርነት ነጋሪት ከመጎሰም እና የሐሰት መረጃ ከመስጠት በመቆጠብ የመፍትሔ አካልነት ሚናችሁን በጥንቃቄ እንድትወጡ ፓርቲያችን በጥብቅ ያሳስባል፡፡  

  1. 6.     ለሃይማኖት አባቶችና ሀገር ሽማግሌዎች፡-
ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፋ ለዚህ የበቃችው በፈጣሪ ጥበቃ፣ በልጆቿ ተጋድሎና በአባቶች ጸሎት ተደግፋ ለመሆኑ ከእናንተ የተሰወረ አይደለም፡፡ ስለሆነም በሀገራችን አሁን የተፈጠረው ውስብስብ ችግር ያለ እናንተ ጸሎትና አባታዊ ተሳትፎ እንደማይሳካ ስለምንገነዘብ ዛሬ ነገ ሳትሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመገናኘት ለችግሩ እልባት በመስጠት ሒደት ግንባር ቀደም ሚና እንድትጫወቱ በታላቅ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

  1. 7.     ለሀገራችን በተለይም በአማራና በትግራይ ክልል ለምትገኙ ወጣቶች፡-
ከአባቶቻችን የተረከብናትን ጥንታዊት ሀገር ከነክብሯና አንድነቷ ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ፤ በትዕግስትና በማስተዋል ብሎም ለአባቶቻችን በመታዘዝ እጅ ለእጅ ተያይዘን ከአጋጠመን ችግር እንድንሻገር ከስሜት ተላቃችሁ የነገዋን ኢትዮጵያ መፃኢ ሁኔታ አገናዝባችሁ ለሰላም ዘብ እንድትቆሙ ፓርቲያችን ይጠይቃል፡፡

  1. 8.     ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፡-
በአሁኑ ሰዓት ባለው ወቅታዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ የማንም የውጭ ሀይል ጣልቃ ገብነት ሳይስፈልጋት ችግሯን የመፍታት አቅሙና ጥበቡም እንዳላት ብቻ ሳይሆን ጉዳዩ የሀገር ውስጥ ጉዳይ በመሆኑ ይህን እውነታ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብልን እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ አልፎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሉዓላዊነት የማያከብርና በአድሎ የተሞላ ጫና እንቃወማለን፡፡

የእናንተ ባልተገባ ሁኔታ ችግሩ ውስጥ ገብቶ ለማማሰል መሞከር እሳቱ ላይ ቤንዚን ከማርከፍከፍ በስተቀር የሚፈይደውና የሚቀይረው ነገር እንደሌለ በውል እንድትረዱት እንጠይቃለን፡፡ ሆኖም እንደ ሁልጊዜው የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር በጠበቀ ሁኔታ ችግሩ እንዲፈታ ከመንግሰት ጎን ቆማችሁ የበኩላችሁን የወዳጅነት እገዛ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

 

 

 

 


Share

Published

By Stringer Report

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
"አገር የደም ዕንባ ማንባቷ እንዳይቀጥል ለሰላም የሚዘረጉ እጆች አይዛሉ” እናት ፓርቲ | SBS Amharic