“ፍትህ ምንድነው” በሚል ጥያቄ መነሻ ስለፍትህ ማብራሪያ የጀመሩት ስትሮንግ፤ ስለእኩልነት ብቻ ሳይሆን ስለፍትሀዊነት ማሰብ አለብን ብለዋል፡፡ የዓለም ማህበረሰብ በተፈጥሮ መጎዳት ከፍተኛ ተጽዕኖ እየደረሰበት መሆኑን ሬጂና ስትሮንግ አጥብቀው ይናገራሉ፡፡
ከሰው ልጅ አኗኗር ጋር በተገናኘ በተፈጥሮ ላይ ጉዳት እየደረሰ በመሆኑ እየደረሰ ስላለው ጉዳትና አጥፊዎች ላይ መወሰድ ስላለበት እርምጃ በትኩረት መታሰብ አለበት ብለዋል፡፡
የአካባቢ ተቆርቋሪዋ ሬጂና የተፈጥሮ እንክብካቤ ሃሳብን ለማስረጽና ለውጥ እንዲመጣ የአስተሳሰብ ችግር መቀረፍ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ ለተፈጥሮ ፍትህን መጠየቅ አዲስ ሀሳብና እንግዳ ስለሆነ የእኛን አስተሳሰብ ለሌላው ማስገንዘቡ ፈተና ነው ብለዋል፡፡ በመንግስት አሰራር ዘንድም በተለመደው ሂደት የመጓዝ አዝማሚያም እንደዋና ችግር መታየት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ በበርካታ አገራት የሚስተዋለው ስለ ተፈጥሮ ደህንነት የመንግስት አሰራርና መረጃ ውሸት የበዛበትና ረጅም ጊዜ የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

Regina Strong. Source: Zoom Meeting
ለረጂም ዓመታት በተቆርቋነትና በተፈጥሮ ጉዳዮች አስተሳሰብ ለመቅረጽ ሲሰሩ የቆዩት ሬጂና ስትሮንግ አሁን በሚችጋን የአካባቢ፣ሀይቆችና ኢነርጂ ክፍል በመንግስት መዋቅር እየሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በሚሰሩበት ሚችጋን የአካባቢ፣ ሀይቆችና ኢነርጂ ክፍል መቋቋሙ በራሱ ትልቅ እምርታ እንደሆነም ያምናሉ፡፡ በአካባቢው ካሉት የመንግስት ሃላፊዎች ጋር በአካባቢ ጉዳዮችና ሀይቆች ጥበቃ ዙሪያ በቁርኝት እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ሬጂና ስትሮንግ በሚሰሩበት ክፍል በዋናነት የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ በሁለት ዓመት ውስጥ ለተፈጥሮ ፍትህን ማረጋገጥ እንዲቻል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት እንደተሰጠ ገልጸዋል፡፡ በተለይ የመንግስት ሰራተኞች ስለአካባቢ ደህንነትና ለተፈጥሮ ፍትህ መረጋገጥ ዓለምአቀፍ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስልጠና እየሰጡ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ በዚህም 49ኛው የሚችጋን ገዢ ዊትሜር ሁሉም ሰራተኞች ስልጠና እንዲወስዱ ማዘዛቸውንም አስታውሰዋል፡፡
መንግስት በመሰል ስራዎች የመሳተፉን አስፈላጊነት አስመልክቶ ለተነሳላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሬጂና ስትሮንግ የተፈጥሮ ፍትህ መዛባት የሚስተካከለው በመንግስት ተሳትፎ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ “መቀየር ያለባቸውን ህጎችና መፍትሄዎች በውይይትና በምክክር ለመቀየር እንሰራለን፤ መንግስት በፍትሃዊ መፍትሄዎች መሳተፍ አለበት፡፡ በየደረጃው ያለው መንግስት አካል እና በዋናነት ከከባቢ ብክለት ስማቸው የሚነሳው ባለኢንዱስትሪዎች ለተፈጥሮ ፍትህን በማረጋገጡ ሂደት በግንባርቀደምትነት መሳተፍ ይገባቸዋል” ብለዋል፡፡

Source: Zoom Meeting
በታዳጊ ሀገራት የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለሚወስዱ ኢንቨስተሮችም አስቀድሞ በአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች የቁጥጥርና ክትትል ስርአት መዘርጋት እንዳለበት የገለጹት ሬጂና ስትሮንግ ይህም እንዲተገበር ማህበረሰቡና መንግስት ለአካባቢ ደህንነት ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
አሁን ባለንበት የኮሮና ዘመን የሀይል አቅርቦትን በተመለከተ በተለይ ለድሃው ማህበረሰብ ድጋፍ ታደርጋላችሁ ወይ በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ትኩረት የሰጠነው በሁሉን አቀፍ መንገድ እንዴት ለማህበረሰቡ እንድረስና ምን እናቅርብ ለሚለው ሀሳብ ነው ብለዋል፡፡
አሜሪካ በተለይ የአረንጓዴ ህጎችን በተመለከተ ስላላት ተሞክሮና አተገባበር ሀሳብ እንዲሰጡ ከጋዜጠኞች የተጠየቁት የተፈጥሮ ተቋርቋሪዋ ሚችጋንን ምሳሌ በማድረግ ህግ አውጭዎች ጋር ሙከራዎች እንዳሉና መሻሻል ያለባቸው ብዙ ጉዳዮች እንዳሉ አንስተዋል፡፡ ህግ አውጪና ህግ አስፈጻሚ አካላት ላይ ክትትል እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡
የተፈጥሮን ክብካቤ በተለያዩ ጊዜያት የማህበረሰብ ንቃት ለመፍጠር በሚንቀሳቀሱ ወቅት ከህግ በላይ ሁነው የተፈጥሮን መብት የሚጥሱ እንደሚገጥሟቸው የተናገሩት ሬጂና ስትሮንግ ቢሆንም ግን ተስፋ መቁረጥ እንደማይገባ ይናገራሉ፡፡ “አሁንም አሁንም ማስተማር ማስተማር ማስተማር ይገባል” ነው የሚሉት፡፡

Regina Strong (L) and Gretchen Esther Whitmer (R). Source: Zoom Meeting
ሚዲያዎች እውነተኛ ታሪኮችን ለሰው ልጆች መንገር እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ወደፊት ለሚያራምዱ ታሪኮች ትኩረት መደረግ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ “ትኩረት ሁሉ ለፍትህ … ለምድር… ለተፈጥሮና … ለሰው ልጆች” ብለዋል፡፡
ደመቀ ከበደ