የሀገር ህልውና እና የዜጎች ደህንነት መጠበቅ የሁሉም ነገር መሠረት ነው!

በሰሞነኛው ብጥብጥ የደረሰው የበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊና የትውልዱ ማፈሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መቀመቅ እየወሰደን እንደሆነ ሕዝብና መንግሥት ከበቂ በላይ ትምህርት አግኝተዋል ብለን እናምናለን፡፡

Ethiopian Citizens for Social Justice

Source: Courtesy of EZEMA

በቅርቡ በልጃችን አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እና ይህን ተከትሎ በሀገራችን በደረሰው የንፁሃን ዜጎች ሞትና የንብረት ውድመት የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለፅን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ መፅናናትን እንመኛለን፡፡

በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት ምክንያት ሁላችንም ሀዘን እና የልብ ስብራት ውስጥ እንዳለን ግድያውን ተከትሎ የደረሠው የበርካታ ዜጎቻችን ሞትና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ሀዘናችንን እጅግ መራር አድርጎታል። የአርቲስቱ ግድያ እና እሱን ተከትሎ በብዙ ዜጎች ሕይወት እና ንብረት ላይ የደረሰው ጥፋት እጅግ አሳሳቢ፣ አሳፋሪ እንዲሁም በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተወገዘ እና በሀገራችን በምንም ዓይነት ሊደገም የማይገባው ድርጊት ነው፡፡

ኢትዮጵያውያን ከአምባገነናዊ አገዛዝ ነፃ ለመውጣትና የሚመጥነንን ሕዝባዊ አስተዳደር ለመትከል ረጅም ጊዜያትን በትግል አሳልፈናል፣ ብዙ ዋጋም ተከፍሏል። ዋጋ የተከፈለባቸው ሙከራዎች የከሸፉ ቢሆኑም በዚህ ሁሉ የታሪክ ውጣ ውረድ ግን የሀገር ህልውና በዚህ መልኩ ተፈትኖ አያውቅም።

ሀገራችን ከነችግሮቿ ዘመን ተሻጋሪ ታሪክ ያላት፣ የምናወሳቸው እና የምንዘክራቸው ዛሬ ላለው ትውልድ መኩሪያ እና መመኪያ የሆኑ የማንነታችን መገለጫዎች የሞሉባት ሀገር ናት፡፡ በአንድ ወቅት አርቲስ ሃጫሉ እንደተናገረው ኢትዮጵያችን በብዙ የማንነት ቀለማት ኅብር የተዋበች ሀገር ናት። ኢትዮጵያዊነታችን በልዩነት ውስጥ የተጋመደ አንድነት መሆኑ ሃቅ ሆኖ እያለ የዘውግ ማንነት እና የቋንቋ ልዩነቶችን እየመዘዙ በሀገር አንድነት ላይ አደጋ መጣል ማንም አሸናፊ ወደማይሆንበት የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንደሚከተን ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን ግልፅ ሆኗል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት አስርተ ዓመታት በተለይም በሕወሃት/ኢህአዴግ ከፋፋይ አገዛዝ ስር ያሳለፈችው የፖለቲካ ትርክት ምን ያህል አደገኛ እንደነበር በግልፅ አይተናል። የሕውሃት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ምንም እንኳን ያረጀና በሕዝብ ትግል የተሸነፈ ቢሆንም፤ የተከላቸው መርዘኛ ቅራኔዎች በአጭር ጊዜ የሚነቀሉ አልሆኑም። እያየን ያለነው የንፁሃን ዜጎች ሕይወት መቀጠፍ እና በረጅም ጊዜ ድካም የተገነቡ ሀብቶች ውድመት የዚሁ አገዛዝ ቅሪቶች እንጂ የኢትዮጵያዊያን እሴቶች አለመሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡

በሰሞነኛው ብጥብጥ የደረሰው የበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊና የትውልዱ ማፈሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መቀመቅ እየወሰደን እንደሆነ ሕዝብና መንግሥት ከበቂ በላይ ትምህርት አግኝተዋል ብለን እናምናለን፡፡ በኢዜማ እምነት እውነተኛ ፌዴራሊዝም ሁሉም ራሱን በራሱ የማስተዳደር እና በመረጠው የመተዳደር መብት እንደሆነ እያስረገጥን ፖለቲካችን ከዘውግ እና ከሃይማኖት ካልተላቀቀ በስተቀር መጨረሻችን እጅግ አደገኛ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ነበር።
በሰሞነኛው ብጥብጥ የደረሰው የበርካታ ዜጎች ህይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመት እጅግ አስከፊና የትውልዱ ማፈሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ በዘውግ ማንነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መቀመቅ እየወሰደን እንደሆነ ሕዝብና መንግሥት ከበቂ በላይ ትምህርት አግኝተዋል ብለን እናምናለን፡፡
በዘውግ እና በሃይማኖት ልዩነት ላይ የተንጠለጠለ የፖለቲካ አካሄድ ወደ መጠፋፋት እየወሰደን መሆኑን በመገንዝብ በማስተዋል እና በመረጋጋት እንድንጓዝ፤ በአንድ ሀገር ለውጥን ማዋለድ ብዙ ትግልና መስዋትነትን የሚጠይቅ እንደዚሁም ከፍተኛ ትዕግስትና ማስተዋል የሚሻ መሆኑን በተደጋጋሚ ስንገልፅ ብንቆይም ይህ አቋማችን ባንዳንድ ወገኖች እንደመለሳለስ ሲቆጠር ቆይቷል።

ሰሞኑን በተከሰተው ቅስም ሰባሪ ጥፋት በሀገራችን ፖለቲካ የሚከተሉትን አበይት ነጥቦች በተለየ እንድንታዘብ አስገድዶናል፡፡ እነዚህም፦

  •  በድንገት የሚፈጠር ነውጥ ሀገራችንን ከማትወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ሊያስገባት እንደሚችል፣
  •  በዘውግ እና በሃይማኖት ላይ የሚሰበክ የፖለቲካ ትርክት፤ ከዚህ ትርክት ተነስቶ የሚቆሠቆሰው ፍጹም ስሜታዊ ጥላቻ እና ጥላቻው የሚቀሰቅሰው የደቦ እንቅስቃሴ፤ የሰውን ልጅ ከሰብዓዊነት ማማ አውርዶ ወደ አውሬነት ሊቀይረው እንደሚችል ተገንዝበናል። በሌላ መልኩ ደግሞ በዚህ ዓይነት ፍጹም ስሜታዊ ሁኔታም ውስጥ ብሔራቸውን እና ሃይማኖታቸውን ተሻግረው፤ ለሰብዓዊነት እና ለጋራ ህልውናችን ዘብ ቆመው፤ በሁከቱ ምክንያት ለችግር የተዳረጉ ዜጎችን በመሸሸግ እና በማስጠለል የንፁሀንን ነፍስ የታደጉ የምንኮራባቸው ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን፣ ይህንን የመሰለው ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያዊያን እሴት ቢፈተንም በዚህ ዘመንም መቀጠሉን፣
  •  ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጭምር እንደገለፁት ችግር ፈጣሪዎች በመንግሥት አስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ የሚገኙ ኃይሎች ጭምር መሆናቸውን፤
  •  ችግሩ በተከሰተበት ጊዜ የመንግስት የፀጥታ ኃይሎች በአንዳንድ አካባቢዎች የዜጎች ሕይወት በአደባባይ ሲቀጠፍ፣ የሀገር ሃብት ሲወድም አይተው እንዳላዩ የማለፍ ሁኔታ እንደነበር፤ የዚያኑ ያክል ደግሞ የሕግና የሞራል ኃላፊነታችውን በመወጣት እየሞቱና እየቆሰሉ ማኅበረሰቡን ከጥቃት የተከላከሉ ብዙ የጸጥታ ኃይሎችን ያየንበት መሆኑ፣
  •  በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ በወታደራዊው የደርግ አገዛዝ ውድቀት ማግስት የፀጥታ ኃይሎች ባልተደራጁበት እና ከፍተኛ የመንግሥት አስተዳደር ክፍተት በነበረበት ወቅት ነዋሪው ለሰላምና መረጋጋት አኩሪ አሰተዋፅኦ እንዳበረከተ ሁሉ፣ ዛሬም ሕዝባችን በመኖሪያ ቀዬው ራሱን በማደራጀት ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ንብረቱን እና አካባቢውን ለመጠበቅ ያሳየው ቁርጠኝነት እጅግ የሚመሰገን ተግባር ሆኖ ጎልቶ መታየቱ፤ ከሰኔ 22 በኋላ በጉልህ የታዘብናቸው ክስተቶች ነበሩ።
በቅርቡ የተከሰተው እና የሀገርን አንድነት የተፈታተነው አውዳሚ ክስተት ለጊዜውም ቢሆን መክሸፉ ችግሩ ዘላቂ የሆነ መፍትሄ አግኝቷል ማለት አይደለም። የሀገራችንን አንድነት የሚፈታተኑ ብዙ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እንደ ተፎካካሪ ድርጅቶችም ሆነ እንደ ዜጎች ያለብን ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ማወቅና በተግባር ለማሳየት መዘጋጀት ይጠበቅብናል።

የሀገርን አንድነት እና ሰላም ባጭር ጊዜ፤ ለዘላቂው ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ምስረታ፤ ከምሩ የቆመ መንግሥት እስካለን ድረስ (በተለያዩ የፖለቲካ እና የፖሊሲ አመለካከት የምናምን የፖለቲካ ድርጅቶችና ዜጎች ብንሆንም እንኳን) ይህን ማዕከላዊ መንግሥት ለማዳከም፤ በዚህም የተለያዩ የጦር አበጋዞች የሚርመሰመሱበት የርስበርስ ግጭት ውስጥ ሊዳርጉን የሚፈልጉ ኃይሎች የሚያደርጉትን ዘመቻ በማስቆም በኩል ሙሉ ትብብር ማድረግ እንዳለብን ልናውቅ ይገባል። በእነኝህ አንኳር ጉዳዮች ላይ የምንስማማ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች የሲቪክ ማኅበረሰብ ተቋማት እና አባላት ለሀገራችን መኖር እና ለሕዝቧ ሰላም ባንድነት በተግባር መቆም እንደሚኖርብን መገንዘብ ያለብን ጊዜ ላይ ደርሰናል።

ኢዜማ በሀገር አንድነትና በማኅበረሰባችን ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር የለበትም ብሎ ያምናል። እነኝህን ሁለት መሰረታዊ እሴቶች በዋናነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ደግሞ ሀገራዊ መንግሥቱ ነው። ያለ ሀገር ፖለቲካም ሆነ ዴሞክራሲ ትርጉም የላቸውም። ለዘላቂው የሀገር አንድነት እና ሰላም ከዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ መኖር፤ ከፍትህ መኖር፤ ከዜጎች እኩልነት መረጋገጥ...ወዘተ ጋር በጥብቅ የተቆራኙ መሆናቸውን እናምናለን።
ኢዜማ በሀገር አንድነትና በማኅበረሰባችን ሰላም ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ድርድር መኖር የለበትም ብሎ ያምናል።
ስለሆነም ሁሉም የሀገራችን ዜጎች ይህን ፈታኝ ጊዜ በትግስት፣ በማስተዋልና በጥንቃቄ እንዲሻገሩት እና የሀገራችንን አንድነት እና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ሁላችንም ያለብንን ኃላፊነትና ድርሻ የመወጣት ግዴታ እንዳለብን በማሰብ ኢዜማ በሚከተሉት ወሳኝ ነጠቦች ላይ በድርጅታችን መርሆዎች ላይ የተመሰረተ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፤

1. የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጥረት በመሆኑ በተለይም ፈታኝ ጊዜያትን ያሳለፈው፣ ከፍጥረታት ልቆ የቆየው እና ተፈጥሮን ገርቶ ትውልድን ማስቀጠል የቻለው በተለያዩ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አቅም ፈጥሮ በመተጋገዝ ነው። በአደረጃጀቱ አያሌ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችን ተቋቁሞ አሳልፏል፤ ከእነዚህም አደረጃጀቶች መካከል «መንግሥት» ትልቁ የሰው ልጅ አደረጃጀት ሲሆን በውስጡ በርካታ አደረጃጀቶችን እንደያዘ ግልፅ ነው፡፡

 የእነዚህ አደረጃጀቶች ዋና መሠረት ደግሞ የቆየው ማኅበራዊ አደረጃጀት ነው፡፡ በሀገራችንም በርካታ የቆዩ የአደረጃጀት ዓይነቶች አሉ፡፡ ይህንን ማጠናከር የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ በእጅጉ ይረዳል የሚል እምነት አለን። ማኅበራዊ ፍትህ በነገሰባቸው በርካታ ሀገራት በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነፃ ማኅበራዊ አደረጃጀቶች አሉ። እኛም ሀገር ሰሞኑን በተፈጠረው ችግር ሕዝቡ በየመኖሪያ ቀዬው ተደራጅቶ ሰላሙን ሲያስከብር ተመልክተናል፡፡

በተለይም በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ ከተሞች የታየው አደረጃጀት ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ሁሉንም የሀገራችንን ማኅበረሰቦች አቅፋ የምትኖር፤ በዓለማችን በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ እንደመሆንዋ በውስጧ ያቀፈቻቸው ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባትና ልዩልዩ አስተሳሰቦችና እምነቶች ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ ናት። ይህን መሰሉ ማኅበራዊ እሴት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት እናምናለን፡፡

ይሁን እንጂ ሰሞነኛው ክስተት እንደሀገር ለከፍተኛ ውርደት የዳረገን የታሪካችን ማፈሪያ ሆኖ አልፏል። በሌላ በኩል የአዲስ አበባ ሕዝብ ዘመኑን በሚመጥን እና በሠለጠነ መንገድ በዘውግ ማንነት፣ በሃይማኖት ወይም በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳያደርግ በመደራጅት ቤተሰቡን እና አካባቢውን ከጥፋት ከመከላከሉም ባሻገር ከተማዋን እጅግ ከከፋ ውድመት ታድጓታል፡፡ ለዚህም አክብሮት እና ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን።

ይህን ዓይነቱ መሰባሰብ ለወቅታዊ ችግሮች ብቻ ሳይሆን ለዘላቂውም ጭምር ጠቀሜታው የጎላ ስለሆነ የማኅበረሰቡ የቆዩ አደረጃጀቶች እንዲበረታቱ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን እየታዩ ያሉ አደረጃጀቶችን በየአካባቢው በሕዝብ በሚመረጡ አካላት ማጠናከር፣ እውቅና መስጠት እና የፀጥታ ጉዳይን በሚመለከት አደራጃጀቶቹን ከማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ እና የመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር የማጣመሩን ተግባር መንግሥት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተቻለ ፍጥነት ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡

አደረጃጀቶቹ የጋራ ደህንነትን ከመጠበቅ በተጨማሪ የከተማዋ ምልክት የሆነውን ሁሉም ዓይነት ማንነቶች ተከብረውባት፣ ዜጎች ተጋግዘው እና ተባብረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን በቀጣይነት ለማረጋገጥም የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አደራ እንላለን። እነዚህ አደረጃጀቶች በሌሎች ኃይሎች እንዳይጠለፉ እና ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ደህንነታቸውን ከመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ጋር እንዲያስጠብቁ ከማስቻል ያፈነገጠ ዓላማ ማስፈፀሚያ መሣሪያ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባም ልናሳስብ እንወዳለን።

2. የደህንነት እና የፀጥታ ተቋማት ዋና ተግባር የሀገርን ደህንነት እና የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅ ነው፡፡ ሰሞኑን ሀገራችን በገባችበት ችግር ዙሪያ ማብራሪያ ሲሰጡ የነበሩ የፀጥታ ተቋማት ኃላፊዎች ችግሩ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ የዘገዩት በሆደ ሰፊነት የፖለቲካውን ምህዳር ለማስፋት መንግሥት በያዘው አቋም ምክንያት መሆኑን ሲገልፁ ሰምተናል፡፡ ይህ ተቋማዊ ኃላፊነታቸውን የዘነጋ አካሄድ እና አገላለፅ በቶሎ ሊታረም ይገባል፡፡ የዜጎችን ሕይወት እና ንብረት ለከፋ አደጋ ዳርጎ ሆደ ሰፊነት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መነገር የለበትም፡፡ ይህንን የማድረግ መብትም ሆነ የሕግ ድጋፍም የላቸውም። የፀጥታ ተቋማት በየደረጃው ተቀናጅተው በመሥራት እና ሀገርን እና ዜጎችን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጥቃት መታደግ ነው ዋና ተልዕኳቸው፡፡ በተለይም በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ሕዝብን በማስተባበር አደጋ ከመድረሱ ቀድሞ የማክሸፍ ሥራ በመሥራት፤ አንዴ ከተፈጠረ ደግሞ በፍጹም ቁርጠኝነት ሀገርን እና ሰላማዊ ሕዝብን ከጥቃት መከላከል የፀጥታ አካላት ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ተግባር እንደሆነ በአንክሮ እንገልፃለን።

3. ለዘመናት የታገልንለት ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነት ሀገርን እና ሕዝብን ለአደጋ እስከሚያጋልጥ ልቅነት ድረስ መሆን እንደሌለበት ደጋግመን ስንገልጽ ቆይተናል፡፡ አሁን እንደምናየው የግል የብዙሃን መገናኛዎች የተወሰኑት በፓርቲ ልሳንነት፣ የተወሰኑት ደግሞ በጥቅም አሳዳጅነት ሀገርን እና ዜጎችን አደጋ ላይ ሲጥሉ ሥልጣን የተሰጠው አካል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ነበረበት፤ አለበትም። ከዚህ አንፃር የግል ብዙሃን መገናኛዎች የሀገሪቱን ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር ጠብቅው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን። በሌላ በኩል የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ደግሞ ሚዛናዊነት በጎደለው መልኩ በተለይም የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ቃለመጠይቆችን ብቻ በማስተናገድ መሪ አዘጋገብ እና ፍረጃ ውስጥ መግባታቸው የዜጎችን በፍርድ ቤት ጥፋተኛነታቸው እስኪረጋገጥ ድረስ እንደነፃ የመታየት መብት የሚጋፋ እና የፍትህ ተቋማቱን አካሄድ የሚያዛባ በመሆኑ ባሰቸኳይ እንዲያርሙት እናሳስባለን።
የግል ብዙሃን መገናኛዎች የሀገሪቱን ሕግና የሙያውን ሥነ-ምግባር ጠብቅው እንዲሠሩ ጥሪ እናቀርባለን።
የመገናኛ ብዙሃን እንዲመሰረት የምንፈልገውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መርህ የተከተሉ፤ የሕዝብ መረጃ ማሳወቂያ፣ ማስተማሪያ እና ማረጋጊያ መሆን እንሚገባቸውም በአፅንዖት እንገልፃለን፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሰረት የብዙሃን መገናኛ ተቋማትን በቅርበት እየተከታተለ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድም አበክረን እናሳስባለን።
የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊነት በጎደለው አዘጋገብ እና ፍረጃ ውስጥ መግባታቸውን እንዲያርሙ እናሳስባለን።
4. የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመስረት ለዘላቂ ሀገራዊ መረጋጋት መሠረት መሆኑን እናምናለን። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመሰረተውም በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማለትም በእውነተኛ ውይይትና ድርድር ብቻ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ዘመናዊ፣ የሠለጠነ ፖለቲካ እና የጨዋታ ሜዳውን ህግ ያከበረ አካሄድ መከተል ይገባናል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደምም ሆነ ሰሞኑን የተከሰተው የመገዳደልና የመጠፋፋት ፖለቲካ ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ የሚወስደን ሳይሆን ከዚህ ቀደም ዋጋ ወደከፍልንባቸው የተወሳሰቡ ችግሮች ውስጥ መልሶ የሚዘፍቀን አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሁሉም ድርሻ አስፈላጊ ቢሆንም በሀገር አንድነት፣ በሰላማዊ እና በሠለጠነ የፖለቲካ ትግል እንዲሁም ወደዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግርን ከሚያምኑ ወገኖች ጋር ለሚደረግ ውይይት ገዢው ፓርቲ ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ በአንድ በኩል የሀገርን ህልውና እና የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቁን አጠናክሮ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሽግግር እውን ለማድረግ የሚያስችል እና ለሁሉም ተሰፋ የሚሰጥ የባለድርሻዎች ውይይት ሳይውል ሳያድር እንዲጀመር እንጠይቃለን፡፡

5. የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት በአጠቃላይ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፤ በተለይ ደግሞ እንደኛ ሀገር ፖለቲካችንን ሰቅዞ ከያዘው የዘውግ ፖለቲካ ወደ ጤናማ የሀሳብ ፖለቲካ በማሸጋገር እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖራቸው ሚና እጅግ የጎላ እና ሚዛንን ማስጠበቅ የሚያስችል እንደሚሆን ይታመናል። ባለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሙያ ማኅበራት በገዢው ፓርቲ ተፅዕኖ ስር የወደቁ እና ተዳክመው የቆዩ መሆናቸውን እንረዳለን። ረጅም ጊዜ ከቆየ አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረግ ሽግግር ውስጥ ለረጅም ጊዜ የተጠራቀሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሁሉ በቶሎ እንዲፈቱ መጓጓት እና ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን እና ፍላጎቶቻቸውን የሚያቀርቡበት እና እንዲመለስላቸው ጫና ለማሳደር ኃይልን የቀላቀለ መንገድ መከተላቸው ትልቅ ተግዳሮት ይፈጥራል። የሙያ እና የሲቪክ ማኅበራት ራሳቸውን ከነበረባቸው ጭቆና ነፃ አውጥተው እና ተጠናክረው የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እና ተደራሽ የሆኑ ብዙሃን መገናኛዎችን በመጠቀም ስለ ሰላማዊ ተቃውሞን የማሰሚያና ጫና የማሳደሪያ መንገዶች በሰፊው በማስተማር ከሕዝብና ከእውነት ጎን ቆመው ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር መረጋጋት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ እናቀርባለን።

6. በሀገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ፖለቲካዊ ሽፋን እየተሰጣቸው ከተነሱ ረብሻዎች ጋር በተያያዘ በርካታ የንፁሃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ሲቀጠፍ እና የግል ባለሃብቶችም ንብረት በሚያሳዝን ሁኔታ ሲወድም እየተመለከትን ነው። እነዚህ ረብሻዎች እንዳይከሰቱ፣ ከተከሰቱም የሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ አደጋ እንዳያደርሱ መቆጣጠር እና የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ዋነኛ የመንግሥት ሥራ በመሆኑ፣ መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቀርቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ መጠየቅ እና ከዚህ በኋላ እንደዚህ ዓይነት ጥፋት በፍፁም እንደማይደገም ቃል ሊገባ እና ሊያረጋግጥ ይገባዋል።
መንግሥት ኃላፊነቱን በሚገባ ሳይወጣ ቀርቶ ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ ወጥቶ ይቅርታ መጠየቅ ይገባዋል።
መንግሥት የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ እና የአርቲስቱን ሞት ተከትሎ ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ጉዳይ ባስቸኳይ አጣርቶ ፍትህ እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባል። እንደዚሁም የሀገራችን ኢኮኖሚ ዳዴ በሚልበት በዚህ ፈታኝ ወቅት ባለሀብቶች አንጡራ ሃብታቸውን አፍስሰው የገነቧቸው መሠረተ ልማቶች እንደዘበት ወድመው፣ ተቃጥለው እና ሠራተኞች ተበትነው ማየቱ እጅግ ያሳዝናል፡፡ በቀጣይም ሃብታቸውን አፍስስው ሊያለሙ የሚችሉ ባለሃበቶችም ዋስትና ስለማይኖራቸው መዋዕለ ንዋያቸውን ከማፍሰስ ይታቀባሉ። ከዚህ አንፃር በሰሞኑ ክስተት ቤት ንብረታቸውና ትልልቅ የንግድ ተቋሞቻቸው ለወደመባቸው ዜጎች መንግሥት ተገቢውን ካሳ ከፍሎ እንዲያቋቁማቸው አበክረን እንጠይቃለን፡፡

በመጨረሻም አሁን ያለንበት ሁኔታ ለሀገራችን እጅግ ፈታኝ መሆኑ ግልፅ ነው። ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ከዕለት ዕለት እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ከአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም በተለይም ከህዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ ግብፅ የፈጠረችው እሰጥአገባ ያመጣው ጫና ከሀገራችን አልፎ የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያውያንም በእነዚህ አንገብጋቢ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከምንግዜውም በላይ በጋራ መቆም የሚገባን ትክክለኛው ሰዓት ላይ እንገኛለን፡፡

በመሆኑም የውስጥ ልዩነቶቻችንን በሠለጠነ ፖለቲካ አሰታርቀን እንደሀገር የተደቀኑብንን ተደራራቢ ፈተናችዎች በፅናት ማለፍ ካልቻልን ለትውልድ የምትሆን ሀገር ማሻገር ይቅርና እኛ ራሳችን ከማንወጣው የከፋ አዘቅት ውስጥ ገብተን እንደምንዳክር መረዳት ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም የሕግ የበላይነትን በማክበር፣ በወንድማማችነትና በእህትማማችነት በመተባበር እና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት አሁን ካለንበት ውስብስብ ችግር ወጥተን ሀገራችንን ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በጋራ እንድናሻግር ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም


Share

Published


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service