በአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑ 23 ኢትዮጵያውያን በእሥር ላይ የሚገኙ የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራር አባላት ተፈትተው በመጪው አገር አቀፍ ምርጫ መሳተፍ እንዲችሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥር 9 2013 በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ጠየቁ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ፤ የለውጡ መከሰት ፈንጥቆላቸው የነበረውን ተስፋ አሁን አሳድሮባቸው ያለውን ቅሬታ ሲገልጡ "ባልደራስን በመሳሰሉ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርሰውን መድሎ እና ጫና ይቀንሳል የሚል ትልቅ ተስፋም ነበር:: ነገር ግን መንግስት ችግሩን ከምንጩ የሚቀርፍ መፍትሄ እና መዋቅራዊ ለውጥ ከማድረግ ይልቅ ውስጣዊ ችግሮች እንዲባባሱ እያደረገ ይገኛል። ለዚህ አንዱ ማሳያ በባልደራስ አመራሮች ላይ የተጀመረው መሰረት አልባ ክስ እና የፍትህ መጓተት ነው። የፍርድ ሂደቱን እጅግ በተራዘመ እና ፈፅሞ አሳማኝ ባልሆነ መልኩ በማጓተት አመራሮቹን ከምርጫ ውድድር ውጭ ለማድረግ መሞከር፣ ለሀገራችን ተጨማሪ ችግር ከመፍጠር ውጭ የሚያስገኘው አዎንታዊ ውጤት አይኖርም" ብለዋል።
አያይዘውም "በእነ እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የባልደራስ አመራሮች ላይ እየተፈፀመ ያለው የፍትህ ጥሰት በሀገራችን የተጀመረውን የለውጥ እና ዲሞክራሲ ሂደት በእጅጉ ይጎዳል ብለን እናምናለን" በማለት አዎንታዊ ምላሽ የሚሹ ባለ አራት ነጥብ ጥያቄዎቻቸውን አቅርበዋል።
1. በሰላማዊ ታጋይነቱ አለም አቀፍ እውቅና የተቸረው አቶ እስክንድር ነጋና የባልደራስ አመራር አባላት አሳማኝ ባልሆነ የክስ ይዘት ለእስር መዳረጋቸው አግባብ ባለመሆኑ፣ ባፋጣኝ ከእስር ተለቀው በመጭው ምርጫ መሳተፍ እንዲችሉ እንዲደረግ እንጠይቃለን::
2. መጭው ምርጫ እንዳለፉት የሕወሃት አገዛዝ ዘመን “ምርጫዎች” በሀይልና ማጭበርበር የሚካሄድ ሳይሆን፣ ነፃ፣ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን እንጠብቃለን:: በመሆኑም በምርጫ ዝግጅቱ ወቅት ሕግና ስርዐቱን አክብረው በሰላማዊ መንገድ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶችና አባላት ላይ የሚካሄደው ኢፍትሃዊ ተጽዕኖ እና ማግለል እንዲቆም እንጠይቃለን::
3. የኢትዮጵያ ሕዝብ አምርሮ የታገለው የሕወሃት ሀይል ቢደመሰስም፣ የዘረጋቸው አፋኝ ሕግጋትና ጎሳ/ብሄርን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም የአገራችንን አንድነት እና የዜጎችን አብሮነት በእጅጉ እየተፈታተኑት ይገኛሉ። ስለሆነም ህወሃትን አስወግዶ አገር አፍራሽ የሆነውን መርዛማ ስርዓቱን እና አስተሳሰቡን ማስቀጠል፣ ህወሃትን ለመደምሰስ ሕዝብ በነቂስ ወጥቶ የከፈለውን መስዋዕትነት ማርከስ እንደሆነ ይሰማናል:: ስለዚህ የሕውሀት ሌጋሲ የሆኑት ህገ መንግስቱ እና የጎሳ ፌደራሊዝሙ ተወግደው በዜግነት መብትና ግዴታ ላይ የተመሰረተ፣ የሀገርን አንድነትና ዘላቂ ህልውና በሚያስጠብቅ ዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ስርአት እንዲተካ አስፈላጊ የሆኑ ተቋማዊና ህጋዊ የለውጥ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እንጠይቃለን::
4. በተለያዩ ክልሎች ማንነትን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች ምክንያት ውድ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን፣ ጥቃቶቹ በአስቸኳይ እንዲቆሙ፣ ወንጀለኞቹም ለሕግ እንዲቀርቡ እና መንግስት ለተጎጂ ወገኖች ተገቢውን ካሳ እንዲያደርግ እንጠይቃለን:: በተጨማሪም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ያልቻሉ እና ዜጎች ለዘር ተኮር ጉዳት እንዲዳረጉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እጃቸውን ያስገቡ የመንግስት አመራሮች ባስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን::
ሙሉ ስም የሚኖሩበት ሃገር
ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ዩኤስ አሜሪካ
ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ገብርዪ ወልደሩፋኤል ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ሞገስ ወልደሚካኤል ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አክሎግ ቢራራ ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አሰፋ ነጋሽ ኔዘርላንድስ
ዶክተር ወንድሙ መኮንን ብሪታኒያ
ፕሮፌሰር ግርማ ብርሃኑ ስዊድን
ዶክተር ተድላ ወልደዮሃንስ ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ሰማህኝ ጋሹ ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ፍጹም አቻምየለህ ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር አብርሃም ጥበቡ ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ልዑልሰገድ አያሌው ካናዳ
አቶ ሙሉጌታ አያሌው ዩኤስ አሜሪካ
አቶ ሃይለገብኤል አያሌው ዩኤስ አሜሪካ
አቶ ጌታነህ ካሳሁን ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ሃምሳሉ አስናቀ ዩኤስ አሜሪካ
አቶ ሙሴ እንግዳሸት ዩኤስ አሜሪካ
አቶ መስፍን አማን ኔዘርላንድስ
አቶ ማስተዋል ደሳለው ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ካሳ አያሌው ዩኤስ አሜሪካ
ፕሮፌሰር ሃብታሙ ተገኝ ዩኤስ አሜሪካ
ዶክተር ብርሃኑ መንግስቱ ዩኤስ አሜሪካ