የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝዳንት አብይ አህመድ ( ዶር ) ለፌደራሉ ተወካዮች ምክር ቤት በተወዳደሩበት የጎማ 2 ምርጫ ጣቢያ ማሸነፋቸውን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
ከዶር አብይ ጋር የተወዳደሩት ከእናት ፓርቲ አቶ ዳግም ዋሪሶ እና ከኢዜማ ደግሞ ካሊድ ጀማል ናቸው።
ቦርዱ እንዳስታወቀው ዶር አብይ በከፍተኛ ድምጽ ብልጫ ያሸነፉ ሲሆን በምርጫ ክልሉ ከተሰጠው 79 ሺህ 295 ድምጽ ውስጥ ዐቢይ 76 ሺህ 892 ድምጽ አግኝተዋል ብሏል።
በተመሳሳይ በአማራ ክልል ባሕር ዳር ምርጫ ክልል የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ፡ አብን የሥራ አስፈጻሚ አባል እና የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር ዶር ደሳለኝ ጫኔ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ማሸነፋቸውን ቦርዱ አክሎ ገልጿል።
ቦርዱ በዛሬው መግለጫው ሁሉም የምርጫ ውጤቶች ወደ ዋና መስሪያ ቤቱ እንደደረሱለት አረጋግጧል። እያጣራ ውጤቶችን እንደሚያሳውቅም የኮሙኒኬሽን ኃላፊዋ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ተናግረዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]