የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ እንደገለፁት ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም የድምፅ መስጫ ቀን በመሆኑ በእለቱ የተመዘገቡ ዜጎች ሁሉ ድምጻቸውን ለመስጠት ይችሉ ዘንድ እና የደምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ያለምንም የጸጥታ ችግር ይከናወን ዘንድ መስሪያ ቤቶች እንዲዘጉ ተወስኗል ብለዋል።
ሶልያና እንዳሉት የምርጫ የፓለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር አዋጅ 1162/ 2011 አንቀጽ 161 የመተባበር ግዴታ መሰረት ለመንግስታዊ እና ለማንኛውም መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባው ጠቅሰዋል።
በዚህ መሰረት ዜጎች ዕለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ የፌዴራል እና የክልል ( ከሃረሪ እና ከሶማሌ ክልል ውጪ) መንግስታዊ ተቋማት ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ስራ ዝግ እንዲያደርጉ ፣ ዜጎች እለቱን ለድምጽ መስጫ ብቻ መጠቀማቸው ስለሚያስፈልግ በክልሎች (ከሃረሪ እና ከሶማሌ ክልል ውጪ) እና በፌዴራል የሚገኙ ማንኛውም መንግስታዊ ያልሆኑ እና የግል ተቋማት በተመሳሳይ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዝግ እንዲያደርጉ ተወስኗል።
ይሁንና የአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ ሆስፒታሎች፣ የዕለት ተዕለት አገልግሎት ሰጪዎችም (ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የትራንስፓርት አገልግሎት..) በዝግ ቀናት የሚያደርጉትን አገልግሎት በተመሳሳይ የሚያከናውኑ ሲሆን የመተባበር ግዴታው እነዚህን ተቋማት እንቅስቃሴ መዘጋት አያስገድድም ተብሏል።
ቦርዱ ባወጣው መግለጫ እንደተጠቀሰው የትራንስፖርት አገልግሎት በተለመደው መንገድ የሚቀጥል ቢሆንም ዜጎች ድምጽ ከመስጠት ውጪ ከፍተኛ እንቅስቃሴን የሚፈልጉ ሁነቶችን እና እቅዶችን እንዳይይዙ እና እንቅስቃሴያቸውን ድምጽ ለመስጠት ብቻ እንዲያደርጉ ቦርዱ ጠይቋል።
በሌላም በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በምርጫው ዕለት ዝግ እንደሚሆኑ ሲያስታውቁ "ሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዕለቱ ዝግ ይሆናሉ። እሱንም ለማካካስ ቀጥሎ በሚመጣው ቅዳሜ ወደ ሥራ የምንገባ ይሆናል" ብለዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስአበባ ]