በ5 ክልሎች እና 2 ከተሞች ምርጫውን መታዘቡን ያስታወቀው ታዛቢ ልዑኩ በዘጠኝ ገፅና በ13 አንኳሮች ባዋቀረው ሪፖርቱ ይፋ እንዳደረገው " ምርጫው በብዙ መልኩ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መስፈርቶችን ያሟላና ዴሞክራሲያዊ ነው።" ብሏል።
ምርጫ ቦርዱንም " ግልፅና አሳታፊ ሂደት በመተግበሩ " ያደነቀ ሲሆን የቀድሞዋ ፖለቲከኛና ዳኛ ብርቱካን ሚዴቅሳን ለዚህ የጎላ ሚና እንደተጫወቱ ጠቅሷል። "ምርጫ ቦርዱ ሙያዊና ነፃነቱን የተላበሰ ለመሆን ያደረገውን ተቋማዊ ጥረት ያየንበት ነው " ሲልም መስክሯል።
በምርጫው 53 ፓርቲዎች ተመዝግበው 46ቱ ዕጩዎቻቸውን ለውድድር ማቅረባቸውን ከእነዚህም 17 ያህል ለፌደራል እንዲሁም 29 ኙ ደግሞ ለክልል መወዳደራቸውን እንዳረጋገጠ ጠቅሷል።
የተመረጡ ጣቢያዎች ላይ ምልከታ አድርገናል ያሉት የሪፖርቱ አቅራቢ ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ "ምርጫውን ተዘዋውረን በተመለከትንበት የምርጫ ቦርድን ተቋማዊ ጥንካሬ ተመልክተናል፣ መንግስት ምርጫው ሰላማዊ እንዲሆን አስፈላጊ የጸጥታ እርምጃ ተግባራዊ አድርጓል" ብለዋል። "ድምጽ ሰጪዎች በምርጫው ደስተኛ መሆናቸውንና የፈለጉትን በነጻነት መምረጣታቸውን ነግረውኛል። የመራጮቹ ትዕግስትም አስገራሚ ነበር" ሲሉ አክለዋል።
"ምርጫው ከሞላ ጎደል ሰላማዊ በሆነ መልኩ ነው የተካሄደው። በአንዳንድ ቦታዎች በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ከጸጥታ ጋር ተያይዞ ስጋቶች እና በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎችን የማዋከብ እና የማንገላታት ችግሮች መስተዋሉን" ኦባሳንጆ ገልፀዋል። "የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ መንግስት እና የጸጥታ አካላት ስራቸውን በአግባቡ ቢሰሩም የቁሳቁስ እጥረትና የመራጮች ብዛት በድምጽ አሰጣጡና በቆጠራው ሂደት ላይ ጫናን ፈጥሯል" ሲሉ ቡድናቸው ያስተዋላቸውን እንከኖች ተናግረዋል የልዑኩ መሪ ኦባሳንጆ።
የሲቪክ ማህበረሰብ አካላት በምርጫው የሚያደርጉትን ተሳትፎ መቀጠልና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከር የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ኦባሳንጆ ጠይቀዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ የትዝብቱን የተጠቃለለ ሪፖርት ከ2 ወራት በኋላ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]