ሰኔ 14 በተካሔደው አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ምርጫ በዕጩዎች ብዛት በሶስተኛ ደረጃ ዋነኛ ፓርቲ ሆኖ የተወዳደረው እናት ፓርቲ ዛሬ ሰኔ 18 2013 ባወጣው መግለጫ "ምንም የጎላ የፀጥታ ችግር ሳይከሰት ምርጫው በማለፉ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ ያለህ እያልን የምርጫ ውጤት ይፋ እስከሚደረግ ባሉት ቀናትና ከዚያም በኋላ ብዙ መከራንና ስቃይን ያሳለፈ ሕዝባችንና ውድ ሀገራችን ከምርጫና የምርጫ ውጤት ጋር ተያይዞ አንዳችም ቀውስ እንዳይፈጠር የፓርቲያችን የጸና አቋም መሆኑንና በዚህም ዙሪያ አበክረን እንደምንሠራ አንገልጻለን" ብሏል።
አክሎም፤ በምርጫው ዕለት የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከተከፈቱበት ሰዓት ጀምሮ ፓርቲው በተወዳደረባቸው የተለያዩ ክፍለ አገራት ያጋጠሙ ችግሮችን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳሳወቀና በማጠቃለያም ባለ17 ገጽ ሪፖርት ማቅረቡን ጠቅሷል።
በዋነኛነት ገጠሙኝ ያላቸውን ቅሬታዎችም እንደሚከተለው ዘርዝሯል።
- የመንግስት ሓላፊዎች እንዲሁም “ስልጠና ተሰጣቸው” የተባሉ ወጣቶች ምርጫን በማስተባበር ሰበብ በምርጫው ዕለት ከፍተኛ የሚባል ቅስቀሳ አድርገዋል፣ በመርዳት ሰበብ የመራጮችን ድምጽ ለማስቀየር ተንቀሳቅሰዋል (በአብዛኛው የምርጫ ጣቢያዎች የታየ)፤
- ከ20 የሚበልጡ ታዛቢዎች ከ45 ደቂቃ እስከ 3 ቀናት ድረስ በእሥር አሳልፈዋል፣ ታዛቢዎቻችን እንዳይታዘቡ በምርጫው ዋዜማ ማስፈራራት ደርሶባቸዋል፣ የአስፈጻሚነት እና ታዛቢነት ባጅ ተቀምተዋል፣ ከ100 በላይ ታዛቢዎች እንዳይታዘቡ ተባርረዋል፤
- በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ተቀያይረዋል፣ ከነአካቴውም ጠፍተዋል (ለማሳያ ያህል ሳይንት 1፣ ዳሞት ጋሌ 1፣ ዋድላ፣ ንፋስ ስልክ ወረዳ 12 ምርጫ ጣቢያ 11፣ ደሴ ፒያሳ ምርጫ ክልልና ጣቢያዎች)፤
- ሁለት ሰው መመረጥ በሚገባው የምርጫ ክልል መመሪያ ተሰጥቶናል 4 ሰው ነው የምትመርጡት በሚል የአስፈጻሚዎች የተዛባ መረጃ አዲስ አበባን ጨምሮ በምዕራብ ጎጃም፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ቡታጅራ በሁሉም ምርጫ ክልሎች በቆጠራ ወቅት ብዙ ደምጽ መስጫ ወረቀቶች ውድቅ እንዲሆኑ አድርጓል፤
- በብዙ የምርጫ ጣቢያዎች የአካባቢ ሚሊሻ ከፍተኛ ወከባ ሲያደርስ ውሏል (ደቡ ጎንደር፣ ሰ/ሸዋ)፤
- ገዥው ፓርቲ መራጮችን 1 ለ 10 በማደራጀት የድምፅ አሰጣጡ በግልና ምሥጢር ሳይሆን በተወካይ አንድ ሰው ለ 10 ሰዎች ጭምር ድምጽ የሰጠባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ፤
- አግባብ ያልሆኑ ተጨማሪ ምርጫ ጣቢያዎች ተከፍተዋል (ወላይታ ሁምቦ 2)፤
- የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ተከፍተው አድረዋል (ላይ ጋይንት 1 እና 2፣ ቢቸና፣ ጎንደር)፤
- ብልጽግና ፓርቲ በተሸነፈባቸው ጣቢያዎች ታዛቢዎች አንፈርምም በማለት ጥለው መውጣትና ሆን ተብሎ በግርግር ውጤት እንዲቀየር ለማድረግ ጥረት ተደርጓል (ምሳሌ ጎንደር እስቴ 3)፤
- በአለቀ ሰዓት የተጨመረው እስከ ምሽት 3፡00 ድረስ የተገፋ የድምፅ መስጫ ሰዓት ለገጠሩ ከባድ ውጤት ይዞ የመጣ መሆኑ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ፓርቲው አያይዞም፤ የምርጫውን ውጤት ስለመጠበቅና ቀጣይ ምርጫዎችንም አስመልክቶ ጥሪውን ሲያቀርብ "በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እንደሚፈጸም እንጠብቃለን፡፡ ውጤቱ ለሕዝብ ይፋ በሚደረግበት ወቅት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ አሁን ስናደርግ እንደነበረው የሰከነ አካሄድ፣ ሓላፊነት በተሰማው መልኩና ሕዝባችንን ለየትኛውም ዓይነት አደጋ የሚያጋልጥ ሥራን ላለመሥራት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንድናደርግና ከምርጫው ውጤት ጋር ተያይዞ ምንም ዓይነት ችግር እንዳይከሰት፣ ጳጉሜን 1 የሚደረጉ ቀሪ ምርጫዎችንም በትዕግስት እንድንጠብቅ ጥሪያችንን ልናስተላልፍ እንወዳለን" ብሏል።