የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሶልያና ሽመልስ አሁን በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች የታየው የመራጩ ህዝብ ተሳትፎ የላቀ እንደነበርና ይህም ቦርዱን በትክክል ድምፄን ይቆጥርልኛል የሚል እምነት እንዳሳደረ የሚያሳይ ነው ብለዋል። ሶልያና ድምፅ የሰጠውን ህዝብ ቁጥር ከየስፍራው አደራጅተው በቅርቡ እንደሚያሳውቁ የገለፁ ሲሆን በትናንትናው ዕለት በተለያዩ አካባቢዎች ቦርዱ ባደረገው ቅኝት ረጅም ሰልፎች ከጠዋት እስከ ምሽት ድረስ መታዘባቸውን ገልፀው በዚህም ቦርዱ ለቀጣይ ስራው ብርታት ሆኖታል ፡ ተዓማኒ ተቋም ለመመስረት የምናደርገውን ጥረት የሚያጎላ ነው ብለዋል።
ሶልያና አብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት መግለፅ እንደጀመሩም ለጋዜጠኞች አረጋግጠዋል። ይሁንና የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት እንጅ የምርጫ ክልሎች ውጤቶች ገና በመገለፅ ላይ ባለመሆናቸው የጣቢያዎቹን ድምር በራሳቸው አስልተው እየገለፁ ያሉ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በአፅንኦት አሳስበዋል።
ሶልያና እንዳሉት የምርጫ ክልሎች ውጤቶች የሚታወቁት ምርጫ ጣቢያዎቹ ለየአቅራቢያዎቻቸው የምርጫ ክልሎች ልከው ከተደመረ በኋላ ሲሆን ገና ቆጠራዎች ያልተጠናቀቁባቸው ጥቂት ጣቢያዎች ያሉ በመሆናቸውና ብዙዎቹም ውጤቶቻቸውን በየጣቢያዎቻቸው ቢያሳውቁም ለምርጫ ክልሎቹ ገና እየላኩ በመሆናቸው የአሸናፊዎች ውጤት እንደታወቀ ተደርጎ መነገሩ ህዝብን ለመረጃ መምታት ያጋልጣል፣ ይህ ሊቆም ይገባል ብለዋል።
በሌላ በኩል ትናንት የምርጫ አስፈፃሚዎቹ የፀጥታ ስጋት አለብን በሚል የተዘጋው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ አምቦ የሚገኝ ምርጫ ጣቢያ እስካሁን አልተከፈተም ብለዋል። በዚህ ጉዳይ የቦርዱ ውሳኔ ምንድን ነው በሚል ከSBS ዘጋቢ የተጠየቁት ሶልያና አሁንም ቁሳቁሶቹ ታሽገው እንደተዘጋባቸው ሲሆን ቦርዱ በቅርቡ ውሳኔውን ያሳውቃል ብለዋል።
በሲዳማ 19 ምርጫ ክልሎች እየተካሄደ ያለው ምርጫም በብዙዎቹ ጣቢያዎች ተጠናቋል ያሉ ሲሆን ቀሪዎቹም በሰዓቱ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል። በተመሳሳይ በጋምቤላ አራት ምርጫ ጣቢያዎችም ድምፅ ሲሰጥ መዋሉን ገልፀዋል።
ትናንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል ህይወታቸው ስላለፈው ዓለም አቀፍ " ታዛቢ " ጉዳይ ቦርዳቸው ስላለው አስተያየት ተጠይቀው በህልፈታቸው ቦርዳቸው ማዘኑን ገልፀው ግለሰቡ የምርጫ ታዛቢ ሳይሆኑ " የክብር እንግዳ ( Guest ) " ነበሩ ብለዋል።
ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ