የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዛሬ ይፋ ባደረገው የ6ኛው አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ውጤት ሰኔ 14/2013 ምርጫ በተከናወነባቸውና ቆጠራው ከተከናወነባቸው 436 የፌደራል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች 410ሩን መቀመጫዎች አሸንፏል።
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ውጤቱን በስካይ ላይት ሆቴል በንባብ አሰምተዋል።
አዲስ አበባን ከአንድ የግል ተወዳዳሪ በስተቀር ሙሉ በሙሉ ብልፅግና ማሸነፉ አስገራሚ ሆኗል።
በዚህ መሰረት በአዲስ አበባ ካሉት 23 መቀመጫዎች 22ቱን ብልፅግና ሲያሸንፍ አንዱን የግል ተወዳዳሪው ዳንኤል ክብረት አሸንፏል።
በአማራ ክልል ምርጫ ከተደረገባቸው 125 መቀመጫዎች መካከል ብልፅግና 114 ቱን ሲያሸንፍ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን 5 መቀመጫዎችን አሸንፏል። በክልሉ አምስት መቀመጫዎች ድጋሚ ምርጫ እንዲከናወን የተወሰነ ሲሆን አንድ መቀመጫ ደግሞ ድጋሚ ቆጠራ የሚከናወን ይሆናል።
በአፋር ክልል ምርጫ ከተከናወነባቸው 6 መቀመጫዎች ሁሉንም ብልፅግና ያሸነፈ ሲሆን
በኦሮሚያ ክልል በ 170 መቀመጫዎች ውድድር የተካሄደ ሲሆን 167ቱን ብልፅግና ቀሪዎቹን ሶስቱን ደግሞ ሶስት የግል ተወዳዳሪዎች አሸንፈዋል።
በቤንሻጉል ብልፅግና ምርጫ ከተከናወነባቸው 3 መቀመጫዎች ሶስቱንም ብልፅግና አሸንፏል። በሌላ መልኩ ሌሎች ሁለት መቀመጫዎች ምርጫው እንዲደገም ተወስኗል።
በተመሳሳይ በጋምቤላ ሶስቱንም መቀመጫ ብልፅግና ያሸነፈ ሲሆን በድሬደዋም ሁለት መቀመጫዎች ምርጫ ተደርጎ አንዱን ብልፅግና ሲያሸንፍ በአንዱ ግን ድጋሚ ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል።
በደቡብ ክልል ምርጫ ከተከናወነባቸው 85 መቀመጫዎች 75 ቱን ብልፅግና፣ 4 ቱን ኢዜማ እንዲሁም 2ቱን የጌዴኦ ህዝብ ዴሞክራቲክ ድርድት ፓርቲ አሸንፈዋል። በክልሉ በሶስት ድጋሚ ምርጫ እንዲሁም በአንድ ደግሞ ቆጠራ በድጋሚ እንዲከናወን ተወስኗል።
በአዲሱ የሲዳማ ክልል ደግሞ በ19 መቀመጫዎች የተደረገውን ምርጫ ሁሉንም ብልፅግና አሸንፏል።
በዚህ አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ከፍተኛውን ድምፅ ብልፅግና ያገኘ ሲሆን ከተቃዋሚዎች አብን በአማራ ክልል፣ ኢዜማና የጌዲዮ ህ/ዴ/ድ/ፓ ደግሞ በደብብ ክልል የፌደራሉን ፓርላማ በጥቂት ወንበሮች ተቀላቅለዋል። እንዲሁም 4 የግል ተወዳዳሪዎች ( አንድ ከአዲስ አበባና ሶስቱ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል] መቀመጫ አግኝተዋል።
ብልፅግና በክልል ምክር ቤቶች ያሉ መቀመጫዎችንም እንደ ፌደራሉ ሁሉ በከፍተኛ ውጤት አሸንፏል።
ተቃዋሚዎቹ አብን በአማራ ክልል ምክር ቤት 13 ፣ ኢዜማ በደቡብ ክልል ምክር ቤት 10 እና የጌዴኦ ህዴድ 6 ፣ በአፋር ክልል ምክር ቤት የአርጎባ ህዝብ ዴሞክራሲ ፓርቲ አንድ እንዲሁም በጋምቤላ ጋህነን 7 የክልላዊ መቀመጫዎችን አሸንፈዋል።

Source: NEBE
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በብዙ ውጣ ውረድ የተከናወነ ምርጫ ሂደት ቢሆንም በገለልተኝነት የተከናወነና ተቋም ለመገንባት ጥረታችንን ያሳየንበት ነበር ብለዋል።
በመጪው ጳጉሜን 1 /2013 ምርጫ ባልተደረገባቸው እና ባሁኑ ምርጫ እንከን ተገኝቶባቸው እንዲደገሙ የተወሰነባቸው ምርጫ ክልሎች ምርጫ ይከናወናል ያሉት ሰብሳቢዋ ካከናወንነው የተሻለ እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]