ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን የሰጡት ቃለ መጠይቅ በዚህ በጥሞና ወቅት በመገናኛ ብዙሃን እንዳይተላለፍ ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን አሳሰበ።
በማሕበራዊ ሚዲያዎች እየተላለፉ ያሉ የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስሉ መልዕክቶችም መቆም አለባቸው ብሏል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምንም እንኳን ቃለ መጠይቁ የመንግስት የስራ ክንውኖች ላይ ያተኮረና የምርጫ ቅስቀሳ እንዳልሆነ ቢታወቅም በዚህ ጥሞና ወቅት ሊተላለፍ አይገባም።
የቃለ መጠይቁ መተላለፍ ብዥታ እንዳይፈጥር ሲባል ከምርጫው በፊት መተላለፍ እንደሌለበት አቶ መሀመድ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ቃለ መጠይቁ እንዳይተላለፍ የተፈለገው መንግስት በዚህ ዓመት የተሻለ ምርጫ እንዲካሄድና ፍትሀዊ እንዲሆን ፍላጎት ስላለው መሆኑን ተናግረዋል።
ስለዚህ ቃለ መጠይቁን ለማስተላለፍ ማስታወቂያ እየሰሩ ያሉ መገናኛ ብዙሃንም ሆኑ ለማስተላለፍ የተዘጋጁ ከወዲሁ እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ የማሕበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የምርጫ ቅስቀሳ የሚመስሉ መልዕክቶችን እያስተላለፉ ያሉ አካላትም ከድርጊታቸው መታቀብ አለባቸው ብለዋል።
መገናኛ ብዙሃንም ቢሆኑ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት በመጠናቀቁ ቅስቀሳ መሰል ዘገባዎችን ከማስተላለፍ ሊጠነቀቁ ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ባለስልጣን ባወጣው የሰዓት ድልድል መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅመው የተሳካ ቅስቀሳ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
[ENA]