የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በግንቦት ወር 2013 ዓ.ም. በሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የመንግስት አካላት፣ የሲቪል ማኅበራት እና የሚዲያ ተቋማት ሊያከብሯቸው፣ ሊፈጽሟችው እና ሊያስፈጽሟቸው ይገባል ያላቸውን ባለ 6 ነጥብ የሰብአዊ መብቶች አጀንዳ የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ አደረገ።
- ተጨባጭ የሰብአዊ መብቶች እርምጃዎች ቃል ኪዳን
(Pledge for Concrete Human Rights Actions)
በምርጫ የሚወዳደሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና እጩዎች በሙሉ ምርጫውን ካሸነፉ ሰብአዊ መብቶችን ለማክበር፣ ለማስከበር እና ለማሟላት የሚወስዷቸውን ተጨባጭ እርምጃዎች በምርጫ መወዳደሪያ ጥሪ ሰነዳቸው (ማኒፌስቶ) ውስጥ በግልጽ እንዲያስቀምጡ እና በተለይም ለመብት ጥሰት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶችን፣ ሕፃናትን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ ሕዳጣንን፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ በተመለከተ የሚወስዱትን ተጨባጭ እርምጃዎች ለሕዝብ በይፋ እንዲያሳወቁና ቃል እንዲገቡ፤
2. ለሰብአዊ መብቶች በቁርጠኝነት መቆም
(Commitment for Human Rights)
በመንግስት ሥልጣን ላይ የሚገኙም ሆነ ሌሎች እጩዎች እና ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ፤ በአጠቃላይ የምርጫ ሂደቱ ሰብአዊ መብቶችን አክብረው በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ፣ በአባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው የሚፈጸምን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንደማይታገሱ በይፋ እንዲያስታውቁ፤ እንዲሁም በአባሎቻቸው የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ግልጽ የሆነ የውስጥ አሰራር በመዘርጋት ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፤
3. ምርጫው ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ መሆኑን ማረጋገጥ
(Ensuring Gender-Responsiveness of the Election Process)
ምርጫ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ የሚያደርግ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሻሻል ግልጽ አመላካቾች ያሏቸውን ስልቶች በመንደፍ እንዲተገብሩ፣ እንዲሁም ሁሉም ባለድርሻ አካላትም የምርጫው ሂደቶች በሙሉ ለሥርዓተ-ጾታ ምላሽ ሰጪ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ፤
4. የሕግና ፖሊሲዎች ማሻሻያ ቃል ኪዳን
(Pledge for legal and policy reform)
በምርጫው ያሸነፉም ሆነ የተሸነፉ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሁሉም ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ያለውን ውስብስብ የፖለቲካና የሰብአዊ መብቶች ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት፣ እንዲሁም ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ የሕግ፣ የፖሊሲ እና የአስተዳደር ጉዳዮችን ለመፈተሽ እና በሰብአዊ መብቶች መርሆች ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስፈላጊውን የሕግና የፖሊሲ ማሻሻያዎች ለማድረግ በይፋ ቃል እንዲገቡና እንዲተገብሩ፤
5. የመንቀሳቀስ፣ የመደራጀት፣ መረጃ የማግኘትና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማረጋጥ
(Protecting freedom of movement, association, expression, and access to information)
የፌዴራልና የክልል መንግስት አካላት በተለይም የፀጥታ አካላት ተግባራቸውን በገለልተኝነት እና በከፍተኛ ኃላፊነት ስሜት በመወጣት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እና እጩዎች እንዲሁም ሚዲያ እና ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችንም ጨምሮ ያለ ምንም ገደብ፣ ክልከላ፣ አድልዎ፣ አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት ወይም የበቀል እርምጃ በሙሉ ነጻነት የመንቀሳቀስ፣ መረጃ የማግኘት፣ የመደራጀትና ሃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ እንዲችሉ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶቻቸው በሙሉ መጠበቃቸውን እንዲያረጋግጡ፤
6. ከግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ከኃይል እርምጃዎች ሙሉ በሙሉ መቆጠብ
(Fully Refrain from Incitement, Hate Speech and Violence)
ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ሲቪል ማኅበራት እና የማኅበረሰብ አንቂዎች በሁሉም የምርጫው ሂደት በአጠቃላይ ግጭት ቀስቃሽ፣ ጥላቻ እና ለመብት ጥሰት ምክንያት ከሚሆኑ ንግግሮች እና ተግባራት፣ በተለይም ከማናቸውም አይነት የኃይል እርምጃ ፈጽሞ እንዲቆጠቡ
ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹የሰብአዊ መብቶች ጉዳይ በሀገራዊ ምርጫው አጀንዳ እንዲሆን ማድረግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ባለድርሻ አካላት በኮሚሽኑ የተቀመጡትን የሰብአዊ መብት አጀንዳ ነጥቦች አትኩሮት ሰጥተው እንዲመለከቷቸው፣ ቃል እንዲገቡ በጠየቅናቸው ጉዳዮች ላይ የሚገቡትን ቃልኪዳን እንዲያሳውቁ እና በአጀንዳው በተቀመጠው መሰረት ሰብአዊ መብቶችን በማክበር እንዲቀሳቀሱ›› ጥሪ አቅርበዋል።