"የማይካድራ ሲቪል ሰዎች ጭፍጨፋ የግፍና ጭካኔ ወንጀል ነው" - ኢሰመኮ

*** ኢሰመኮ በማይካድራ ጭፍጨፋ "ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime)" ስለመሆኑ ተናገረ።

EHRC - Mai-Kadra

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of Ethiopian Human Rights Commission Source: EHRC

በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው የማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በወቅቱ በስልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሲቪል ሰዎች ላይ  የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል (atrocious crime of massacre against civilians) መሆኑን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው ኮሚሽኑ ከሕዳር 5 እስከ ሕዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ በማይካድራ ከተማ እንዲሁም በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሁመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ባደረገው ምርመራ የደረሰበትን ግኝቶች ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት ነው፡፡

ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል (crimes against humanity) እና የጦር ወንጀል (war crime)  ሊሆን እንደሚችል የሚያመለክት ስለሆነ ኮሚሽኑ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል፡፡

በቀዳሚ ሪፖርቱ እንደተመለከተው በአካባቢው የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ ጸጥታ መዋቅር በፌዴራሉ አገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቅቆ ከመውጣቱ በፊት ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በማበርና በመተባበር በተለይ ‹‹አማሮችና ወልቃይቴዎች›› ያሏቸውን የአካባቢው ነዋሪ ሲቪል ሰዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት በመጥረቢያ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል፡፡

ኢሰመኮ ከአካባቢው ምንጮች እስከ አሁን በአገኘው መረጃ በአነስተኛ ግምት እስከ 600 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ትክክለኛው ቁጥር ከዚህ ሊበልጥም እንደሚችል በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

ሳምሪ የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጅች የሆኑ ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሲቪል ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያን እና በእርሻ ቦታ ደብቀው በመሸሸግ ሕይወታቸውን እንዳተረፉላቸው ኢሰመኮ ያነጋገራቸው ምስክሮች አረጋግጠዋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ‹‹በማይካድራ ከተማ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በብሔር ማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ኢሰብዓዊ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል፤ ስለ ወደፊት በሰላም አብሮ መኖርም ተስፋ ይሰጣል›› ብለዋል፡፡

አክለውም ‹‹የተጐዱ ሰዎችን እና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና ከመጠገን በተጨማሪ፤ በዚህ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

 

 


Share

Published

By Stringer Report

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service