የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰማኮ) ኅዳር 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በትግራይ ክልል እተካሄደ ያለው ውጊያ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አደጋ እንደሚያሳስበውና በጉዳዩ ላይም ከሚመለከታቸው ልዩ ልዩ አካላት ጋር እየመከረ የሚገኝ መሆኑን አስታውቋል።
አክሎም “ግጭቱ አሁን በደረሰበት ደረጃም ቢሆን ለሰላማዊ መፍትሔ የሚደረግ ጥረት አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ” የሰብዓዊ እርዳታና አገልግሎቶች ተደራሽነት (Humanitarian Assistance and Access) ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥቶ አሳስቧል።
የድርጊቱንም አስፈላጊነት ሲገልጥ፡-
· ምግብ፣ መድኃኒት እና የመሳሰሉት አስፈላጊ አቅርቦቶችን ለሲቪል ሰዎች ለማድረስ፤
· በጦርነቱ ሂደት የተጐዱ ሰዎችን ወደ ሕክምና ለማድረስ፤
· በጦርነቱ የተጐዱ አካባቢዎች እና ሰዎችን መልሶ ለማቋቋም፤
· በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ እና መልሶ ለማቋቋም፤
· በአከባቢው ለሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ተገቢውን ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ እንደሆነ አስረድቷል።
ፈጣን ግብራዊ ምላሽ እንዲሰጥም “የሰብዓዊ እርዳታ እና አገልግሎቶችን በአፋጣኝ ተግባራዊ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና/ወይም በፌደራል መንግስት በተለይ የትግራይ ክልልን በተመለከተ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል በአፋጣኝ የሰብአዊ ዕርዳታ ጉዳይ ዴስክ እንዲያቋቁም እና ከሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ምክክር እንዲጀመር ኢሰመኮ ጥሪ ያቀረባል” ብሏል።
በውጊያው ተሳታፊ የሆኑ አካላት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በመከተል የቀይ መስቀል ማኅበር የሰብዓዊ አገልግሎቶቹን እንዲያከናወን ተገቢው ትብብር እንዲደረግለትም አሳስቧል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ስለተከሰቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ስጋቶችና እያከናወናቸው ስላሉ እንቅስቃሴዎቹ ሲገልጥም፤
- ከግጭቱ ጋር በተያያዘ በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት እና በአንዳንድ አካባቢዎች ሰዎች በትግራይ ብሔር ማንነታቸው የተነሳ የማግለል እና መድልዎ አሰራር ደርሶብናል በማለት የገለጹትን መሰረት በማድረግ ኢሰመኮ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ነዉ።
- ለኢሰመኮ ከቀረቡት ጥቆማዎች እና መረጃዎች ሰዎችን በብሄራቸው ማንነት በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ (ethnic profiling) እንዲጋለጡ የሚያደርግ ምክንያታዊ ስጋት መፈጠሩን ስለተረዳን ኮሚሽኑ ይህንንም በቅርበት እየተከታተለ ነዉ።
በማለት የገለጠ ሲሆን፤ አያይዞም “በቅርቡ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጻሚነቱ ወሰን በትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ ስለሆነ፤ በሌሎች አካባቢዎች የሚደረግ የሕግ ማስከበር ሂደት መደበኛውን የሕግ ማስከበር ሥነ ሥርዓት ደንቦች ተከትሎ የሚፈጸም መሆኑን ኢሰመኮ ለማስታወስ ይወዳል” ሲል አስገንዝቧል።