የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው ይህንኑ የመጨረሻ የውሳኔ ሃሳቡን በዚህ ሳምንት መጨረሻ ወይም በመጪው ሳምንት መጀመሪያ ለሚታደመው ምክር ቤት እንደሚያቀርብ ይጠበቃል።
አጣሪ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ፅድቅ በቸረው የውሳኔ ሃሳቡ ላይ ሁለት ዋነኛ ማብራሪያና የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ዕሳቤዎቹን አስፍሯል።
- በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54 (1)፣ 58 (3) እና 72 (3) ላይ የተደነገገው የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ከአንቀጽ 93 እንዲሁም ከሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች፤ ዓላማዎችና ግቦች ጋር በማገናዘብ የኮቪድ - 19 ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል ፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ጸንቶ በሚቆይባቸው ጊዜያትና ከተነሳም በኋላ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የስልጣን ርክክብ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል በማለት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84 (1) መሠረት የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።
2. የኮቪድ - 19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ወረርሽኝ ዓለም አቀፍና የጤና ድርጅቶች የሚያወጡትን መረጃ መሠረት በማድረግ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የሳይንሱ ማኅበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበትና ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሔድ በማለት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84 (1) መሠረት የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት የውሳኔ ሃሳብ አቅርቧል።