የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ሀገራዊ ምክርቤት አንደኛ አመት ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባዉን ከመስከረም 29/2013- ጥቅምት 1/2013 ዓ.ም ሲያካሂድ በወቅታዊ የኢትዮጵ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የሰላም መደፍረስ ጉዳዮች ላይ በስፋትና በጥልቀት መክሯል፤ ፓርቲው የሚተገብራቸውን የተለያዩ መመሪያዎች፣ እንዲሁም የ2013-2017 ዓ.ም የፓርቲዉን የአምስት አመት ስልታዊ ዕቅድና የ2013 ዓ.ም የአንድ አመት እቅድ በስፋት እና በጥልቀት በመመርመር ወደተግባር እንዲገቡ በሙሉ ድምጽ ዉሳኔ ካሳለፈ በኋላ የሚከተሉትን የአቋም መግለጫዎች አዉጥቷል፡፡
1. ሁሉንም ተግባራት ማከናዎን የሚቻለዉ በሀገሪቱ አራቱም ማእዘኖች ሰላም ሲኖርና የህግ የበይላነት ሲከበር መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነዉ፤ ነገር ግን በመላ ኢትዮጵያ ሀገሪቱን ለ27 አመታት ሲዘርፍና የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመንፈግ እንደፈለገ ሲያስር ሲገድልና ሲያኮላሽ የነበረዉ ዘረኛዉ ህዉሀት ከጠቅላይ አምባገነንቱ ተባሮ መቀሌ ከመሸገበት እና በዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራዉ‹‹ የለዉጡ ቡድን›› መንግስታዊ ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ በርካታ ሁነቶች ተከስተዋል፡ ፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ እጅግ ዘግናኝ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ነፍስ ባላወቁ እምቡጥ ህጻናት ሳይቀር በጽንፈኛ ብሄርተኞችና እነሱ በሚደግፏቸዉ ታጣቂ ቡድኖች፤ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ል (በተለይ በመተከል በተደጋጋሚ) እንዲሁም በደቡብ እስካሁን ድረስ እየተፈጸሙ ነዉ፡፡ ዜጎች በገዛ ሀገራቸዉ እንደሁለተኛ ዜጋ እየታዩ ሀብት ንብረታቸዉ እየተዘረፈና እየወደመ፣ ከመኖሪያ ቀያቸዉ እየተፈናቀሉ ነዉ፡፡ ኢሕአፓ ከዚህ በፊት ባወጣቸዉ ተደጋጋሚ አቋሞቹ እንደገለጸዉ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ያሳየዉ ቸልተኝነትና፣ መዘግየት እነዚህ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊቶች እንዲፈጸሙ በር እንደከፈተ ያምናል፡፡
ስለዚህ ሉአላዊነታችንንና የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ሀገራዊ ሰላምን የማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነነት የመጠበቅ ሃላፊነት ያለባቸዉን የተለያዩ የጸጥታ መዋቅሮች የሚመራዉ መንግስት ስለሆነ አሁን የጀመረዉን ህግ የማስከበር ስራ አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በአጥፊዎችም ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተለይም በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ መሽገው የዜጎችን ህይወት የሚቀጥፉ ህገወጥ ታጣቂ ቡድኖች ላይ ትጥቅ የማስፈታት እና ወደህግ የማቅረብ፤ በወንጀል ድርጊት ያልተሳተፉትን አጣርቶ ወደ ሰላማዊ ኑሮቸዉ እንዲመለሱ የማድረግ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ ይጠይቃል፤ ፓርቲያችን ኢህአፓም ጸረሰላም ሀይሎችን በጽናት ታገላል ፡
2. በሃገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት በርካታ ዓመታት የሚፈጸሙት ዘግናኝ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መጣስ መንስኤው በዋነናት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ–መንግሥት ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጧል፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት፣ የጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ አስተዳደርም ሕገ–መንግሥቱን ለማሻሻል በተደጋጋሚ ቃል ገብቶ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
ነገር ግን፣ ያ ሁሉ ቃል–ኪዳንና ያ ሁሉ የጠ/ሚ/ሩ ንግግር ወደጎን ተትቶ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ውይይት ወቅት ይታያል ተብሎ የነበረው ሕገ–መንግሥት ምንም ዓይነት ማሻሻያም ሆነ ማስተካከያ ሳይደረግበት ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሁሉ ዋነኛው መንስኤ እንደሆነ አለ፡፡ ኢሕአፓ ኢትዮጵያ ውስጥ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ ለሚፈጸሙት ግፎች ሁሉ የመጀመሪያው ተጠያቂ ይህ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ–መንግሥትና ይዘቱ ስለሆነ አስቸኳይ ማሻሻያ እንዲደረግበት መንግሥትን ይጠይቃል፡፡
3. በተጨማሪም፣ የጠ/ሚ/ር አብይ አስተዳደር በተደጋጋሚ ይደረጋል እያለ ቃል–ሲገባ የነበረው የብሔራዊ ዕርቅና የሃገራዊ መግባባት አጀንዳ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ አጀንዳ እንደሆነ ኢሕአፓ ጽኑ እምነት አለው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙት ሕጋዊና ሠላማዊ የሆኑት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የሚሳተፉበት፣ ሃገራዊ መግባባትን ትኩረቱ ያደረገ የፓርቲዎችና የሲቪክ ማኅበራት የጋራ መድረክ አስፈላጊነት ሳይታለም የተፈታ በመሆኑ፣ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥት ለዚህ አጀንዳ ቅድሚያ ሰጥቶ የውይይትና የድርድር መድረኩ በአፋጣኝ እንዲካሄድ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
4. በያዝነው የ2013 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ይካሄዳል የተባለውና የሚጠበቀው 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ ሕጋዊና ሠላማዊ ሆኖ እንዲተገበር ኢሕአፓ ከፍተኛ የሆነ ፍላጎት አለው፡፡ በመሆኑም፣ ምርጫ የአንድ ቀን ተግባር ሳይሆን የብዙ ወራትን የመደራጀትና የማደራጀት ተግባራት ከያንዳንዱ የፖለቲካና የሲቪክ ማሕበር የሚጠይቅ ክንውን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ግን፣ ከ5ኛው ሃገራዊ ምርጫ ማግስት ጀምሮ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት ሠላምንና ጸጥታን ማስከበር ተስኖት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ እየተከሰተ ይገኛል፡፡
በዚህ ያለመረጋጋትና የሠላም ዕጦት ውስጥ ሆኖ ምርጫን የሚያክል ከፍተኛ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግም አጅግ አዳጋች ነው፡፡ በመሆኑም፣ መንግሥት ሁሉም ዜጎች በሕግ–ፊት እኩል የሚሆኑበትንና የሚዳኙበትን የፖለቲካ–ኢኮኖሚ ምሕዳር አስፍቶ የዜጎችን በሕግ የበላይነት ሥር ብቻ የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲያከናውኑ የማድረግ ኃላፊነቱን በተግባር እንዲወጣ ኢሕአፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
5. በየጊዜዉ እያሻቀበ ያለዉ የዋጋ ግሽበትና በኮቪድ 19 መከሰት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ የጨመረዉ ስራ አጥነት የዜጎችን የእለት ተእለት ኑሮ በሰቆቃ የተሞላ አድረጓል፣ ከዚህ በተጨማሪ ባሳለፍነዉ 2012ዓ.ም በተከሰቱ ሰዉሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችም ለከፋ የርሀብ አደጋ ተጋላጭ ሁነዋል፡፡ በመሆኑም ኢሕአፓ፤ መንግስት በረዥም ጊዜ ለዜጎች በተለይም ለወጣቶች በርካታ የስራ እድል መፍጠር የሚችሉ ሀገር በቀል ኢንቨስትመንቶችን እንዲያስፋፋ፣ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ እና ህገወጥ የገንዘብ ዝዉዉርን በመቆጣጠር የዋጋ ግሽበቱን ከ2 ዲጂት በታች የሚወርድበትን የኢኮኖሚ አማራጭ እንዲተገበር፣ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸዉም ተገቢዉን ድጋፍ በወቅቱ እንዲያቀርብ በአጽንኦት ይጠይቃል፡፡
6. ከደንቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ወደ ትዉልድ ቀያቸዉ ሲመለሱ ታፍነዉ ተወስደዉ እስካሁን ድረስ ደብዛቸዉ የጠፋዉ ተማሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ የኢሕአፓ የእግር እሳት ነዉ፤ ስለዚህ መንግስት ልዩ ተኩረት ሰጥቶ ተማሪዎቹ እዉነት በህይወት ካሉ የማስመለስ ስራ እንዲሰራ፣አለያም እዉነቱን ለቤተሰቦቻቸዉ፣ ለኢትዮጵያና ለአለም ህዝብ እንዲያሳውቅ ኢሕአፓ የዘወትር ጥያቄዉን ዛሬም ያቀርባል፡፡
7. ኢሕአፓ ሕብረብሔራዊ ፓርቲ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉአላዊነት፣ በህዝቧ ዉህድ ማንንነት የማይጠራጠሩ፣ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለሚያምኑና በህጋዊ መንገድ ለተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ ኑ! ሀገራችን ከገባችበት ጽንፈኛ የጎሳ እና የጥላቻ ፖለቲካ ቅርቃር በጋራ እንታደጋት፤ ሀገራዊ ብሄራዊ መግባባትን በመፍጠርና የፖለቲካ ቁርሾን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምና እድገት የሰፈነባት ሀገር እናድርጋት፤ የሚል የአክብሮት ጥሪዉን ያስተላልፋል፡፡
8. በሀገርቤትና በዉጪ ሀገር ለምትገኙ ቀደምት የኢሕአፓ አባላትና መስራቾች ዘላለማዊ ከሆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ህላዌ ጋር በየጊዜዉ እየታደሰ የሚዘልቅ ዘመን ተሸጋሪ ሀሳብ ያነገበዉ ኢሕአፓ ከዉጪ ሀገር ወደሀርቤት ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሀገሩ ምድር ላይ ትግሉን በጽናትና ቁርጠኝነት እያካሄደ መሆኑን ተገንዝባችሁ ፓርቲያችን ኢሕአፓን በተለያዬ መነግድ በመደገፍና በማጠናከር የትግላችሁን ፍሬ ማፍራት ዕውን ታደርጉ ዘንድ ጥሪዉን ያስተላልፋል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)
ጥቅምት 5 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢሕአፓ ለተሻለ ነገ!