የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ እና መልሶ ማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ እርዳታ ጥሪ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተጠቀሰው ግጭቶች ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ ፣ የአንበጣ መንጋ ፣ ኮቪድ 19 እና ሌሎችም ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች አገራችንን በማወክ ተከታታይ ሰብአዊ ቀውስ አስከትለዋል ተብሏል፡፡
በመግለጫው እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር በታህሳስ 2013 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በምዕራብ፣ ደቡብ እና መካከለኛው ትግራይ፣ በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎ፣ በመተከል፣ በኮንሶ እና ቤንቺ ሸካ አካባቢዎች ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት አጠቃላይ እና ተጨማሪ ምግብ የሚፈልጉ ከ 2.53 ሚሊዮን በላይ ተጋላጭ ሰዎች መኖራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች መጠለያ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች፣ መተዳደሪያ እና ቅድመ ማገገም፣ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታና አምቡላንስ አገልግሎቶች፣ የስነ-ልቦና እና መልሶ ማቋቋም እንዲሁም የቤተሰብ ማገናኘት ድጋፎች፣ በተጨማሪም የጤና ማዕከል ተቋማትን እና የቀይ መስቀል ቅርንጫፎችን ጥገና እና መልሶ መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ለእነዚህ አካባቢዎች በጠቅላላ የሚገመተው የገንዘብ ፍላጎት ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ ነው ፡፡
"አደጋዎች ባሉበት እና ሰብዓዊ ቀውስ በሚከሰትበት ቦታ ሁሉ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሁል ጊዜም ቀድሞ ይገኛል" ያለው መግለጫው ስለሆነም በጎ ፈቃደኞቹንና ሠራተኞቹን በማስተባበር ህይወትን ለማዳን እና ኑሮን ከመጠበቅ አንፃር የተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑንም ገልጧል፡፡
ማህበሩ በ2012 የበጀት ዓመት አምቡላንስ እና የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አገልግሎቶች፣ የምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ዕቃዎች ድጋፍ፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ፣ የቅድሚያ ማገገም እና የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ፣ የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ማገናኘት፣ የኮቪ -19 ዝግጁነት እና ምላሽ ስራዎችን አከናውኗል፡፡
በአጠቃላይ በ2012 ዓ.ም ማህበሩ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ከ36 ሚሊዮን ለሚበልጡ ግለሰቦች ድጋፍ አድርጓል፡፡ በ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ደግሞ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ 138 ሺህ ሰዎችን ደርሷል ብሏል መግለጫው፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ላለፉት ሁለት ወራት የተከሰቱትን ግጭቶች ተከትሎ በትግራይ፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እና ኦሮሚያ በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ200 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች የህክምና፣ የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች አቅርቦቶች፣ መጠለያ አቅርቦት፣ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ፣ መልሶ የማቋቋምና የተጠፋፉ ቤተሰቦች የማገኛኘት አገልግሎቶችን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡
ማህበሩ 300 የበጎ ፈቃደኞች እና ሠራተኞችን እንዲሁም 100 አምቡላንሶችን በማሰማራት በቅርቡ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ እና ከዚያ በኋላ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑትን ወገኖች ህይወት ለማዳን እና ኑሯቸውን መልሶ ለማቋቋም በንቃት መሳተፉን አስታውቋል፡፡
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]