የከትግራይ ወደ ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያንን መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል ብሔራዊ ኮሚቴ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ተቋቁሟል።
ጥቅምት 24 - 2013 በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ በሕወሓት የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል የተቀሰቀሰን ውጊያ ተከትሎ የሁመራ፣ ማይ ካድራና በረከት ከተሞች ነዋሪ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ለመሰደድ ግድ መሰኘታቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ለፋና ተናግረዋል።
አምባሳደሩ አያይዘውም ብሔራዊ የመልሶ ማቋቋም ኮሚቴው ስደተኞቹ ከሱዳን ተመልስው እንዲቋቋሙ የሚያደርግ መሆኑንና አባላቱም በስደት ካምፖች ያሉት የአያያዝ ሁኔታዎችን ለማጥናት ወደ ሥፍራው መጓዛቸውን ገልጠዋል።
መንግሥት ስደተኞቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከሱዳን መንግሥትና የተመድ ከፍተኛ ስደተኞች ኮሚሽን እየሠራና እስከዚያም ከዓለም አቀፍ ምግባረ ሰናይ ድርጅቶች የሰብዓዊ ረድኤት እገዛ የሚያገኙባቸው መንገዶች የሚመቻቹ መሆኑን አምባሳደር ይበልጣል አስረድተዋል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ረድኤት አስተባባሪ ባባካር ሲሴ ተመድ ከተጠበቀው በላይ የስደተኞች ቁጥር መናርን ተከትሎ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ከ200፣000 በላይ ስደተኞችን ለመቀበል ዕቅድ መንደፉን አስታውቋል።
የተመድ ዕቅድ ግብር ላይ ለመዋል በሚያስችል መልኩ ስንዱነቱን በዚህ ሳምንት መጨረሻ የሚያከናውን ሲሆን እስከዚም ድረስ ለ60፣000 ሰዎች የአንድ ወር ቀለብ የሚሆን ምግብ ዝግጁ እንደሆነ አስታውቋል።
አቶ ሲሴ "ቀውሱ የተከሰተው ኖቬምበር 7 ሲሆን በአንድ ሳምንት 20፣000 አሁን ከ30፣000 ሺህ በላይ ደርሷል" ሲሉም የስደተኞቹን ቁጥር በፍጥነት መናር አመላክተዋል።
አክለውም፤ ትግራይ በኮቨድ - 19 በጣሙን ከተጠቁት ክልሎች በሶስተኛ ደረጃ ያለች መሆኑን አመልክተው ስደተኞቹ የሱዳንን ድንበር አቋርጠው ሲዘልቁ ራሳቸውን ከቫይረሱ የሚከላከሉበት ጭምብል ወይም ሌላ ዓይነት መከላከያ አለማድረጋቸውን ገልጠዋል።
ምንም እንኳ ለስደተኞቹ ካምፕ ውስጥ ከገቡ በኋላ ጭምብሎች ቢታደላቸውም የቫይረስ ምርመራ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን አመላክተዋል።