የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት የወታደራዊ ግዳጃ አፈጻጸሙን ለማቀልጠፍ ሁለት ተጨማሪ ዕዞችን መመስረቱን በትናንትናው ዕለት በብዙኅን መገናኛ በኩል አድርጓል።
የሁለት ተጨማሪ ዕዞችን መቋቋም በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ ያስታወቁት የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አደም መሐመድና የሠራዊቱ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ናቸው።
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አዲስ የተቋቋሙት ዕዞች የማዕከላዊና ሰሜን ምዕራብ ዕዞች መሆናቸው ተነግሯል።
ቀደም ሲል ተደራጅተው ያሉት የሰሜን፣ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ዕዞች በአወቃቀራቸው ጸንተው ግዳጃቸውን ማከናወኑን ይቀጥላሉ።
ጄኔራል መኮንኖቹ የአገር መከላከያ ሠራዊቱን አደረጃጀት፣ የማሻሻያ ለውጥ እንቅስቃሴዎች፣ የወቅቱን የፀጥታና ሰላም ሁኔታዎች አስመልክተውም ማብራሪያ ሰጥተዋል።