ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በኮረናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ወቅቱን ጠብቆ እንዳይካሄድ ተስጓጉሎ የነበረውን የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ምርጫ ማካሄድ እንደሚቻል የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክረ ሃሳብ አቀረቡ።
ሚኒስትሯ ምክረ ሃሳቡን ያቀረቡት ለ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ታድሞ ላለውየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው።
በጤና ሚኒስቴር የቀረበው ሪፖርትና ምክረ ሃሳብ፤
- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየቀነሰ ባይሆንም የቅድመ መከላከልና ስርጭቱን በመግታት ሂደት ውስጥ በሁሉም ደረጃ አቅም ማሳደግ መቻሉን
- ወረርሽኙ አሁንም የጤና ስጋት ቢሆንም ቀደም ሲል ከነበሩት ልምዶች እንፃር ከፍተኛ አለመሆኑ
- ኮቪድ-19 በሽታ ረዘም ላለ ጊዜ አብሮን ሊቆይ ስለሚችልና አንፃራዊ በሆነ ሰዓት ምርጫው ሲራዘም ከነበርንበት ሁኔታ ለስርጭቱ የተሻለ መረጃ ያለን በመሆኑ ቀደም ሲል ከነበረበት በተሻለ የመከላከል ሁኔታዎች በመኖራቸው
- የህብረተሰቡ ግንዛቤ መሻሻል በማሳየቱ
- የማስክና የሳኒታይዘር ምርት በሀገር ውስጥ በስፋት በመኖሩ
- የጤና ተቋማት ዝግጁነትና ግብአት አቅርቦት መሻሻሉ
- የምርመራ ኪት ማምረትን ጨምሮ የላቦራቶሪ አቅም ማደግና የዘርፈ ብዙ ምላሽ በተሻለ ሁኔታ የሚገኝ መሆኑ
- እንዲሁም የአገራት የምርጫ ተሞክሮን በማየት የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ሀገራዊ ምርጫን ማካሄድ እንደሚቻል ተመልክቷል።
በዋነኛ ምክረ ሃሳብነትም የሚከተሉትን ቅድመ ሁኔታዎች አሟልቶ አገራዊ ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል የተጠቆመ ሲሆን፤
- ከዚህ በፊት ከነበረው የምርጫ ሂደት በተለየ መልኩ ኮቪድ-19ኝ መከላከልን ከግምት ውስጥ ያስገባ የምርጫ ስነ ምግባር ደንብ እና ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ማዘጋጀትና በተዘጋጁ ዝርዝሮች መሰረት በሁሉም ደረጃ በበቂ ዝግጅቶች ወደ ትግበራ መግባት ያስፈልጋል
- በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የወረርሽኝ ስርጭት ከተከሰተ በተለየ ሁኔታ መታየት ሊያስፈልገው ይችላል
በማለት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንኳር ምክረ ሃሳቦቹን ለተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።