የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛው አስቸኳይ ስብሰባው 6ኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ወሰኗል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ምርጫውን በ2013 ማካሄድ የሚቻልበትን የዓለም ጤና ድርጅትና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክረ ሃሳቦች ተከትሎ ግብር ላይ እንዲውል ለምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳብና ሪፖርት ያቀረቡት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ ናቸው፡፡
የውሰኔ ሃሳቡም የውሳኔ ሃሳብ ቁጥር 16/2013 ሰፍሮ በአንድ ተቃውሞ በ8 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል፡፡
በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ላይ ተጥለው የነበሩት የኮቨድ - 19 ወረርሽኝ ገደቦች ላልተው ክፍት እንዲሆኑ በምክር ቤቱ ውሳኔ ውስጥ ተካትቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ለምክር ቤት የቀረቡትን የሚኒስትሮችና ዳኞችን ሹመት ይሁንታ ቸሯል።
በዚህም መሰረት፦
- ዶ/ር ቀነዓ ያደታ የኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር
- ዶ/ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ
- ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር
- ኢንጅነር ታከለ ኡማ የኢፌደሪ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመሆን በምክር ቤቱ በ5 ድምጸ ተዓቅቦ ገጥሞት በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ40 የከፍተኛ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞችን ሹመት በ5 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምፅ እንዲሁም የ50 የመጀመሪያ ፍርድ ቤት እጩ ዳኞችን ሹማት ደግሞ በ3 ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።