የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እንዲሁም በመድረኩ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ዐቢይ አሕመድ ፓርቲው በምርጫ ወቅት የሚጠቀምበትን ማኒፌስቶና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክትን ይፋ አድርገዋል፡፡
“ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ለጋራ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል የምርጫ 2013 የብልጽግና ፓርቲ ማኒፌስቶ እና የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት ይፋዊ የእውቅና መድረክ በሸራተን አዲስ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በመድረኩ በርካታ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
***
አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ሐረሪ ክልሎች የዕጩዎች ምዝገባ ዛሬ ይጀመራል
ምዝገባው የሚከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለዕጩዎች ምዝገባ ባወጣው ከየካቲት 08 እስከ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነው።
የምርጫ ክልሎቹ በተጠቀሱት ጊዜያት የዕጩዎች ምዝገባ የሚያከናውኑት ለምርጫ ክልል እና ለዞን ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሊያገለግሉ የሚችሉ ቢሮዎችን በማዘጋጀታቸው መሆኑን ቦርዱ ገልጿል።
በአፋር፣ አማራ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ እና ሶማሌ ክልሎች ከየካቲት 05 እስከ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለዕጩዎች ምዝገባ የሚውሉ ቁሳቁሶች እንደሚጓጓዙ እና የዕጩዎች ምዝገባ አስፈጻሚዎች ሥልጠና እንደሚሰጥም ቦርዱ አመልክቷል።
ከየካቲት 15 እስከ 26 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ የዕጩዎች ምዝገባ እንደሚከናወን ቦርዱ ባለፈው ሳምንት መወሰኑ ይታወሳል።
[ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]