የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ጥር 6፣ 2013 መጪውን አገር አቀፍ ምርጫ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “እንደሀገር ያለንበት ሁኔታ እና መጪው ሀገራዊ ምርጫ የሁሉንም ባለድርሻ አካላት በኃላፊነት መንቀሳቀስ እና ሀገራችንን ወደ ተረጋጋ ሁኔታ የምንቀይርበት ሊሆን ይገባል ብሎ” እንደሚያምን አስታውቋል፡፡
ግንቦት 28 የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ያለውን ፋይዳም አስረድቷል፡፡
• የ2013 ምርጫ ተቀባይነት ባለው ሂደትና ውጤት ሊጠናቀቅ የሚችልበት እድል መኖሩ፣
• በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ የምርጫ ፍላጎት ተግባራዊ ሊሆን የሚችልበት እድል መኖሩ፣
• በሀገራችን የሚገኙ ሀገራዊና ክልላዊ ፓርቲዎች፣ ከሕዝብ ሊኖራቸው የሚችለውን ድጋፍ በሠለጠነ የምርጫ ሂደት ውጤት ማወቅ የሚችሉበት ጥሩ ታሪካዊ አጋጣሚ ሊሆን ስለሚችል፣
• ለወደፊት ለሚደረጉ ምርጫዎች ተጨባጭ ልምዶች ማግኘትና ልምዶቹን በመጠቀም የተሻለ ምርጫ ማድረግ የሚቻልበት መልካም አጋጣሚ መሆኑ፣
• በምርጫ አሸናፊ ሆኖ የሚወጣው ድርጅት ከዚህ በፊት በታሪካችን ከነበሩት መንግሥታት በሙሉ ሕጋዊ ቅቡልነት ያለው አካል ሊሆን የሚችልበትም አጋጣሚ መፍጠሩ፣
• ተቀባይነት ያለው የምርጫ ሂደትና ውጤት መሰረት አደርጎ የሚቋቋመው መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ጥቅምና ደህንነትን በሚመለከት ከማናቸውም ሦስተኛ አካል ጋር የሚያደርገውን ስምምነትም ሆነ ውል፣ ከሕጋዊ ቅቡልነት የሚመነጭ፣ ጠንካራ አቅም ሊያገኝ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር መቻሉ ናቸው።
ለምርጫው ስላለው መሰናዶ ሲገልጥም፤ በትራቴጂያዊ ግቦች ካስቀመጣቸው አራት ግቦቹ ውስጥ አንዱ “በምርጫ አሸንፎ መንግሥት መሆን” እንደሆነና ከብሄራዊ የምርጫ ዘመቻው ባሻገር በክልልና በምርጫ ወረዳ ላይ ያሉ የዘመቻ ክፍሎችን በማዋቀር ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
ኢዜማ የፖሊሲ አማራጭ ዝግጅቱን አስመልክቶም እስከአሁን በ18 የፖሊሲ ሰነዶች ላይ ምክክር እንዳደረገ፣ የምርጫ 2013 ማኒፌስቶ ከምርጫው በፊት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
ሰላምና ጸጥታን አስመልክቶ “በትግራይ ክልል ሕወሃት መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት በማድረስ የሀገራችን አንድነት ላይ የጋረጠውን አደጋ ምክንያት መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የተፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል፤ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በተደጋጋሚ እየተከሰተ የሚገኘው የዜጎች ሞትና መፈናቀል፤ በምዕራብ ኦሮሚያ ሁነኛ መፍተሄ ያልተገኘለት የሰላም መደፈረስና በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየደረሰ የሚገኘው እንግልት እና ሞት በታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ሥልጣንን ወደ ዜጎች በማቅረብ፤ እውነተኛና ዘላቂ የሆነ የሕዝብ አስተዳደር፣ ግልፅነትና ተጠያቂነትን የሞላበት የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓትን እና ባህል ለመፍጠር መሰረት የሚጣልበትን ቀጣዩ ምርጫ ላይ ጥላ ያጠሉ ሁኔታዎች ናቸው” ብሏል፡፡
ተፎካከሪ ፓርቲዎችን በተመለከተም “የተወሰኑ ፓርቲዎች መሪዎቻቸው እና አባሎቻቸው በሕግ ጥላ ስር ከመሆናቸው የተነሳ በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ሊሳተፉ እንደማይችሉ እየገለፁ ይገኛል። ኢዜማ የነዚህ ፓርቲዎች በመጪው ምርጫ አለመሳትፍ ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርነው የመጪውን ምርጫ ልዩ ከሚያደርኩት ምክንያቶች አንዱ የሆነውን የሁሉንም ዓይነት አስተሳሰቦች በምርጫው ለውድድር የመቅረባቸውን ዕድል ስለሚቀንስ ምርጫው ያለው አጠቃላይ ፋይዳ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለን እንሰጋለን” አተያዩን ገልጧል።