በሕዳሴ ግድብ ፕሮጄክት ላይ ትንናት ሰኞ ኦገስት 10 ሊካሄድ ተወጥኖ የነበረው የሶስትዮሽ ድርድር በሱዳን የይራዘምልኝ ጥያቄ ለመጪው ሳምንት ሰኞ ኦገስት 17 - 2020 ተሸጋግሯል።
ይህንኑ የድርድሩ ሂደት ለአንድ ሳምንት መስተጓጎልን የገለጠው የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ "አገራቱ [ግብፅና ሱዳን] ድርድሩን በመቀጠል የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ ቢሮ ስብሰባ በተካሄደ ሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የመካከለኛ እና የመጨረሻ ሪፖርት ለሕብረቱ ሊቀመንበር ሪፖርት እንዲያቀርቡ ይጠበቅ ነበር። ሆኖም ግብፅና ሱዳን ባቀረቡት ማራዘሚያ ምክንያት ባለፉት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ድርድር ሳይካሄድ ቀርቷል" ብሏል።
አያይዞም፤ ጁላይ 24 - 2020 የአፍሪካ ሕብረት ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ሐምሌ 27 - 2012 የሶስቱ ተደራዳሪ አገራት የውኃ ሚኒስትሮች በጋራ ታድመው የደረሱበትን መግባባት ተመርኩዞ ኢትዮጵያ "የግድብ ሙሌት ደንብ" ማቅረቧን አጣቅሷል።
ተጨማሪ ያንብቡ

የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሕዳሴ ግድብ ድርድር ተራዘመ
ምንም እንኳ ቀጣዩ ታሳቢ ስብሰባ ስለመካሄዱ የተሰጠ ማስተማመኛ ባይኖርም በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ነሐሴ 11 - 2012 (ኦገስት 17 - 2020) የሶስትዮሽ ድርድሩ ይቀጥል ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የስብሰባውን ፋይዳ አስመልክቶም "በድርድር የሚደረሰበት ስምምነት ብቸኛ አማራጭ በመሆኑ ኢትዮጵያ ለድርድሩ ውጤታማነት አበክራ ትሠራለች" ሲል ገልጧል።
የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስቴር በበኩሉ "ግብፅ የሕዳሴ ግድብን ሙሌትና አጠቃቀም አስመልክቶ ሕጋዊ አስገዳጅነት ካለው ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ ናት" ብሏል።