ዛሬ ረፋድ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ወቅታዊ ጉዳይ መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ አባላት በስካላይት ሆቴል ማብራሪያ እየሰጠ ነው። ማብራሪያውን እየሰጡ የሚገኙት ምክትል ጠቅላይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንና ምክትላቸው አቶ ሬድዋን ሁሴን ናቸው።
አቶ ደመቀ በንግግራቸው "በትግራይ ክልል የተወሰነው የተናጠል የተኩስ አቁም በክልሉ ተጨማሪ ጥፋት እንዳይከሰት በማሰብ ነው" ብለዋል። አቶ ደመቀ አክለውም "በርካታ ሀብቶች የወደሙ በመሆኑ ከዚህ በላይ በሰው ሕይወትና በአገሪቱ ሃብት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት ነው።" ብለዋል።
ጉዳት የደረሰባቸውንና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መንግስታቸው መልሶ ሲገነባ እንደነበረ ያወሱት ምክትል ጠቅላይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በ " ሽብርተኛው ህወሓት" ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰ ነው። ስለሆነም ከዚህ በላይ ሀብት ማባከንና ሕይወት መጥፋት ስለሌለበት ለክልሉ ዜጎች የጥሞና ጊዜ ተሰጥቷል ብለዋል።
"የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን መረዳት ይገባዋል፤ በዚህ ወቅት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የምንጠብቀውም ትብብር ነው" ያሉት አቶ ደመቀ መንግስታቸው በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ እንዲያገኙ ከአጋር አካላት ጋር እንደሚሰራም ተናግረዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]