የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሶልያና ሽመልስ በዛሬው የምርጫ ዋዜማ መግለጫቸው እንዳስታወቁት በአማራ ክልል የደምቢያ ምርጫ ክልል፣ የተሁለደሬ አንድ እና ተሁለደሬ ሁለት፣ በኦሮሚያ ክልል የግንደበረት ምርጫ ክልል እና ነገሌ ምርጫ ክልል የድምፅ መስጫ ቁሳቁሶች ከሰማያዊ ሳጥን ወጥተው ስለተከፈቱ እንዲሁም የግል ተወዳዳሪ ዕጩ ቅሬታ በማቅረቡ ነገ ሰኞ ምርጫ እንዳይካሄድባቸው ቦርዱ መወሰኑን ተናግረዋል።
እነዚህ የምርጫ ክልሎች መቼ ምርጫ እንደሚደረግባቸው ውሳኔ እንደሚሰጥ የገለፁት ሶልያና በተጠቀሱት የምርጫ ክልሎች የተፈፀመውን ወንጀል እንዲጣራ ተደርጎ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

Solyana Shimelis. Source: SBS Amharic/Demeke Kebede
ቦርዱ ከዚህ ቀደም በፀጥታና ሌሎች ምክንያቶች 64 የምርጫ ክልሎች ጳጉሜ 1 /2013 ምርጫ እንዲከናወን መወሰኑ ይታወሳል።
በነገው ምርጫ 9505 የፖለቲካ ፓርቲ ተወዳዳሪ ዕጩዎች እንዲሁም 148 የግል ዕጩዎች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን
13 ፓርቲዎች አዲስ አበባ ፣ 46 ፓርቲዎች ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ይወዳደራሉ።
***
በቅርቡ የተቋቋመውና ሁሉንም የጋዜጠኝነት ተግባራት የሚሰሩ ባለሙያዎች በመላ አገሪቱ አባል ያደረገው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማህበር ምርጫው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ መልካም ምኞቱንና አጠቃላይ የምርጫ ሁኔታውን አስመልክቶ ያወጣውን መግለጫ አውጥቷል፡፡
ማህበሩ ለSBS አማርኛ በላከው በዚህ መግለጫው የነገው ምርጫ ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መንገድ እንዲዘገብና የሚመለከታቸው መረጃ ሰጪ አካላትም ለጋዜጠኞቹ ተገቢውን መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
ራሱን ማህበሩን ጨምሮ በተለያዩ አካላት ሲሰጡ የነበሩት ሙያዊ ስልጠናዎች የምርጫ አዘጋገብንና መረጃ ማንጠርን ታሳቢ ማድረጋቸውን ያስታወቀው ማህበሩ ምርጫውን ለመዘገብ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከወገንተኝነት የፀዱ፣ ሚዛናዊ፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃዎችን እንዲያደርሱ አጽንኦት ሰጥቶ አሳስቧል፡፡ ይህም በሀሰተኛና ቅይጥ መረጃዎች ስርጭት ምክንያት የሚያጋጥሙ ውዥንብሮችን ለማስቀረት የላቀ አበርክቶ ይኖረዋልም ነው ያለው ማህበሩ፡፡
ምርጫ ቦርድ የመረጃ ማጣራት ቡድን ከመመስረት ባሻገር ዕለታዊ መግለጫዎችን ለመስጠት መሞከሩን ያደነቀው ማህበሩ በዘገባ ወቅት ችግር የሚገጥማቸው ባለሙያዎች ካሉ ለሚመለከታቸው የፀጥታ አካላትና ለማህበሩ ጭምር እንዲያሳውቁ ጠይቋል።
በምርጫ ወቅት ከሚታዩ ሂደቶች የድምፅ አሰጣጥ ዋነኛው ነው ያለው ማህበሩ ከ38 ሚሊዮን በላይ ዜጎች (የጳጉሜ መራጮችን ጨምሮ) ለምርጫ ተመዝግበው የሚገኙበትን ምርጫ ለመዘገብ በርካታ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ተዘጋጅተዋል ብሏል። 68 የሚዲያ ተቋማትና 1 ሺ 400 ዘጋቢዎች ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዘጋቢነት ፈቃድ መሰጠታቸውንም ነው የገለጸው።
89 ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፈቃድ ተሰጥቷቸው አገር ውስጥ ገብተው ወደተለያዩ የሃገሪቱ የምርጫ አካባቢዎች መሰማራታቸውንም የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣንን የትናንት መግለጫ ዋቢ አድርጎ አስቀምጧል፡፡
ማህበሩ በቅርቡ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ለተውጣጡ 47 ምርጫ ዘጋቢ ጋዜጠኞች በምርጫ አዘጋገብና መረጃ ማንጠር ዙሪያ ስልጠና መስጠቱ ይታወሳል
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]