የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔውን አስመልክቶም የምክር ቤቱ አፈጉባኤ አደም ፋራህ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ “የሚቋቋመው አስተዳደር በሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች መሰረት የሚሰራና የትግራይን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚያስከብር ይሆናል” ብለዋል።
“ሕገወጡ የህወሓት ቡድን የትግራይ ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የሚከበረው በእሱ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል” ብለዋል። ይህም የሕገ መንግስቱን መርሆዎች የሚፃረር እንደሆነ ነው የገለጹት።
ቡድኑ የፌዴሬሽንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች ውሳኔዎችን በመጣስ ኢ-ሕገ መንግስታዊ በሆነ መንገድ ሲንቀሳቀስ ቆይቶ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት አድርሷል ሲሉም አስታውሰዋል።
በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ቡድኑ ወደ ሕጋዊ መንገድ እንዲመጣ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ የቆየ ቢሆንም ሊመጣ ባለመቻሉ የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ፣ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋምና የፌዴራል የፀጥታ አካል በክልሉ እንዲሰማራ ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል።
በትግራይ ክልል የሚቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በአጭር ጊዜ የሚቋቋም ሲሆን ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግስት ይሆናል ተብሏል።
የሚቋቋመው አስተዳደር የክልሉ ምክር ቤትና ካቢኔ ሲሰራቸው የነበሩ ተግባራትን እንደሚያከናውንም ተገልጿል።
ኢዜአ እንደዘገበው ኃላፊነቱን ለመወጣትም እስከታችኛው መዋቅር ድረስ አስፈፃሚዎችን የሚመድብ ይሆናል ተብሏል።