የ2022 ፌዴራል ምርጫ አብቅቷል። የአውስትራሊያ የምርጫ ኮሚሽን በሚሊየን የሚቆጠሩ ድምፆችን መቁጠር ጀምሯል።
ቆጠራው የተጀመረው መቼ ነው?
ድምፅ መስጠት ያበቃው ልክ 6pm ላይ ነው። ይሁንና በዚያ ሰዓት ድምፅ ለመስጠት ተሰልፈው ያሉ መራጮች ካሉ ድምፅ መስጠት ይችላሉ።
ድምፅ መስጠቱ እንዳበቃ ወዲያውኑ በዕለቱና ቀደም ብለው መራጮች የሰጧቸው ድምፆች ቆጠራ ጀምሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድምፅ ቆጠራ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 151 ወንበሮች ያሉት ሲሆን፤ አብዛኛዎቹ ድምፆች የምርጫ ቀን ምሽት ይቆጠራሉ።
የአውስትራሊያ ምርጫ ኮሚሽን ባለስልጣናት የምርጫ ሳጥኖችን በመክፈት የምርጫ ድምፆችን አራግፈው ታጥፈው ሳጥን ውስጥ የገቡ የምርጫ ወረቀቶችን ይዘረጋሉ። ሁሉም '1' (የመጀመሪያ ምርጫ) ድምፆች በየዕጩዎች ስም ተለይቶ በመቀመጥ ይቆጠራል።
ቆጠራዎቹ የሚካሔዱት በምርጫ ኮሚሽን ማዕከላት ሲሆን ከምርጫው ቀን በፊት የተሰጡ ድምፆች ቆጠራም ይካሔዳል። .
ቀጥሎም የኮሚሽኑ ሠራተኞች ቁጥር 2 የተፃፈባቸውን መቁጠር ይቀጥላሉ።
"ቆጠራው በቀጣይነት አማራጭ ሆነው የተሰጡ ድምፆችንም ያካትታል። ከሁለቱ ዕጩዎች አብዛኛውን አማራጭ ድምፆች አክሎ አብላጫ ድምፅ ያገኘ ዕጩ በመሪነት ይመደባል" በማለት የምርጫ ኮሚሽን ገልጧል።
አክሎም "ሁሌም ቁጥር አንድ ምርጫን በመቁጠር ብቻ ግልፅ ውጤትን ለመግለፅ ስለማይቻል እያንዳንዱን የምክር ቤት ሊያሸንፍ የሚችለውን ዕጩ ለማመልከት ቁጥር አንድና ሁለት የምርጫ ድምፆችን መቁጠር ግዴታ ነው" ብሏል።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቆጠራ
እንደ ምርጫ ኮሚሽን አባባል የላይኛው ምክር ቤት የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ በጣሙን ውስብስብ በመሆኑ በርካታ የጥበቃ እርምጃዎችንና ቆጠራዎችን ግድ ይላል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቆጠራን ተከትሎ የኮሚሽኑ ባለስልጣናት ለእያንዳንዱ ፓርቲ / ቡድን ከመስመር በላይና በታች 1 ቁጥር ያለባቸውን የምርጫ ወረቀቶች ለይተው ያስቀምጣሉ።
ከምርጫ ምሽት በኋላ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የድምፅ ወረቀቶች ተሰብስበውና ታሽገው አንደኛ አማራጭ የሆኑት ወደ ምርጫ ኮሚሽን ማዕከላት ለዳግም ቆጠራ ይላካሉ። ከዳግም ቆጠራ በኋላ ዳግም ታሽገው ወደ ክፍለ አገራትና ግዛት ማዕከላዊ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተቆጣጣሪ ይላካሉ።
ማን አሸናፊ እንደሆነ የሚታወቀው መቼ ነው?
ቅዳሜ ዕለት የትኛው ፓርቲ እንደሚያሸንፍና መንግሥት ማቆም እንደሚችል ማወቅ ይቻላል። ይሁንና የምርጫ ምሽት ውጤት አውስትራሊያውያን የሚያደምጡት የአውስትራሊያ ምርጫ ኮሚሽን ይፋ ውጤት አይደለም።
"የአውስትራሊያ ምርጫ ኮሚሽን ከቶውንም ውጤት የምርጫ ምሽት አስታውቆ አያውቅም፤ ምናልባትም ከቶውንም ይፋ አያደርግም"
"ለሰዎች፣ ለሚዲያ አስተያየት ሰጪዎች፣ ለምርጫ ተንታኞች፣ እርግጥ ነው ለፓርቲዎችና ዕጩዎች አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡበት የቆጠራ አመላካች ውጤቶችን እንሰጣቸዋለን" ሲሉ የምርጫ ኮሚሽን ቃል አቀባይ ኢቫን ኢኪን-ስሚዝ በኮሚሽኑ ድረ ገጽ የቪዲዮ መልዕከታቸው ገልጠዋል።
ያንንም ተከትሎ የሚዲያ አስተያየት ሰጪዎች ወይም ዕጩዎች ራሳቸው የአሸናፊነት ውጤትን የሚገልጡበት ቢሆንም ያ ማለት ግና የምርጫ ኮሚሽን ሕጋዊ ውጤት ነው ማለት አይደለም።
ቃል አቀባዩ የኮሚሽኑ "ይፋ ጠቅላላ ይፋ ውጤት በምርጫው ቀን ማግሥት አይሆንም፤ ከድኅረ ምርጫ ቀናትና ሳምንታት በኋላ እንጂ" ብለዋል።
ከምርጫው ምሽት በኋላ የሚሆነው ምንድነው? በማግስቱ እሑድስ?
እሑድ ዕለት በአብዛኛው ሰዎች በምርጫው ምሽት በጣም የተቀራረበ ውጤት ስላሉባቸው ቆጠራዎች የሚነጋገሩበት ቀን ይሆናል።
አቶ ኢኪን - ስሚዝ የቆጠራ ማዕከላት ውስጥ እምብዛም እንቅስቃሴ እንደማይኖርና ሳይቆጠሩ ያሉ የድምፅ ወረቀቶች በፍጥነት የሚቆጠሩበት ይሆናል ሲሉ ገልጠዋል።
እንዲሁም፤ የምርጫ ኮሚሽን እሑድ ዕለት የምርጫ ወረቀቶችን ማሸግ፣ ማጓጓዝ፣ ምዝገባዎችን ማጣራትና የፖስታ ድምፆችን ማረጋገጫ መስጠት ይሆናል።
እስከ ዓርብ ድረስ የምርጫ ኮሚሽን 2.73 ሚሊየን የፖስታ ድምፅ መስጫ ማምለከቻችዎችን ተቀብሏል፣ ከ 4.6 በላይ አውስትራሊያውያን ከምርጫ ቀን በፊት ድምፅ ሰጥተዋል። በጠቅላላው 7.35 ሚሊየን ሰዎች ከምርጫ ቀን በፊት መርጠዋል።
የምርጫ ኮሚሽን የድምፅ ቆጠራ ምን ያህል ተአማኒ ነው?
የምርጫ ኮሚሽን የምርጫ ምሽት ቆጠራ በፓርቲ ለተወከሉ እምኝ ተወካዮች ሙሉ በሙሉ በቆጠራ ሂደቶች ክፍት ነው። የቆጠራ ውጤቶች ሁሉ በወቅቱ ይፋ ይሆናሉ።
አንድ ፓርቲ ወይም ጥምር ፓርቲዎች አሸናፊ ሆነው መንግሥት ለማቆም ምን ያህል ወምብበሮችን ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል?
ከ 151 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንበሮች ውስጥ አንድ ፓርቲ ወይም ጥምር ፓርቲዎች 76 ወንበሮችን ማሸነፍ ይገባቸዋል። አለበለዚያ አነስተኛ መንግሥት ማቆምን ግድ ይሰኛሉ።
ይህም ማለት ሌብር አብላጫ ወንበር አሸንፎ መንግሥት ለማቆም ሰባት ተጨማሪ ወንበሮችን ማሸነፍ ይጠበቅበታል፤ የሊብራል / ናሽናልስ ጥምር ፓርቲዎች ይዘዋቸው ያሉትን ወንበሮች ጠብቀው መቆየት ይጠበቅባቸዋል።