አንኳሮች
- ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ድምፅ ለመስጠት መሥፈርቶችን የሚያሟሉ ሁሉ፤ ምዝገባ አካሂደው በፌዴራል፣ ክፍለ አገርና የአካባቢ መንግሥት ምርጫዎች ድምፃቸውን ለመስጠት ግድ ይሰኛሉ።
- የኒው ሳውዝ ዌይልስ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫ መረጃን ከእንግሊዝኛ ውጪ ከ20 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ያቀርባል።
- የኦንላይን ምርጫ ሥርዓት iVote በአሁኑ ምርጫ ግብር ላይ አይውልም።
በወቅቱ ፕሪሚየር ዶሚኒክ ፔሮቴይ የሚመራው የቅንጅት መንግሥት መራጮች ለአራተኛ ጊዜ ለአሸናፊነት አብቅተው መንበረ መንግሥቱ ላይ እንዲመልሱት እየጠየቀ ነው።
የአቶ ፔሮቴይ ተቀናቃኝ በመሆን ፕሪሚየር ለመሆን ተፎካካሪ ሆነው ያሉት በ2021 ለፓርቲያቸው መሪነት የበቁት የሌበር መሪ ክሪስ ሚንስ ናቸው።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፓርላማ የሚከተለው 'ባይካሜራል' ወይም የታችኛውን ምክር ቤትና የላይኛውን ምክር ቤት የያዘ 'የሁለት ምክር ቤቶች' ሥርዓትን ነው።
የላይኛው ምክር ቤት 42 የምክር ቤት አባላት የሚመረጡበት ሲሆን፤ 21 የምክር ቤት አባላት በእያንዳንዱ ክፍለ አገራዊ ምርጫ ለሁለት የምርጫ ዘመን የሚያገለግሉ ምክር ቤት አባላት ከስምንት ዓመታት ላላፈ ጊዜ እንዲያገለግሉ ይመረጣሉ።
የፖስታ ድምፅ መስጫ ማመልከቻዎች ለኒው ሳውዝ ዌይልስ የምርጫ ኮሚሽን 5pm ማርች 20 መድረስ ይኖርበታል።
ድምፅ ተሰጥቶባቸው የተጠናቀቁ የምርጫ ሳጥኖችና የድምፅ ምስክር ወረቀቶች ለኒው ሳውዝ ዌይልስ የምርጫ ኮሚሽን ከ 6pm ኤፕሪል 6 ቀን ሳያልፍ መድረስ አለበት።

Chris Minns took on the NSW Labor leadership in June 2021. Credit: AAP / BIANCA DE MARCHI/AAPIMAGE
የምርጫ ቀን ድምፅ አሰጣጥ – ማርች 25
በመላው ኒው ሳውዝ ዌይልስ 2450 የምርጫ ማዕከላት በቤተ ክርስቲያናት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የማኅበረሰብ ማዕከላትና በሌሎች መድረኮች ይሰናዳሉ።
በዕለቱም ማዕከላቱ ከ 8am እስከ 6pm ክፍት ሆነው ይውላሉ።
መራጮች ወደ ምርጫ ማዕከላት ሲዘልቁ፤ በሠራተኞች ስም፣ አድራሻ፣ የምርጫ አካባቢና ቀደም ብለው መርጠው እንደሁ ይጠየቃሉ።
የዝርዝር መረጃዎቹ ትክክለኛነት ከተረጋገጠ በኋላ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች ይሰጣቸዋል።

NSW Premier Dominic Perrottet. Credit: AAP / Bianca De Marchi
ድምፅ መስጠት ግዴታ ነው
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ መሥፈርቶችን ያሟሉና ምዝገባ ያካሄዱ መራጮች በፌዴራል፣ ክፍለ አገርና የአካባቢ ምርጫዎች ድምፅ መስጠት ይጠብቅባቸዋል።
ቤት አልባ፣ የአካል ጉዳተኛ፣ ከፍለ አገር ወይም ባሕር ማዶ ያሉ ከሆነ የድምፅ አሰጣጥ
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ነዋሪ ሆነው ያሉ ቋሚ አድራሻ የሌላቸው፣ የቀውስ መጠለያ ውስጥ ወይም የሽግግር ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች በመራጭነት ሊመዘገቡ ይችላሉ።
በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ድምፅ መስጥ ያልቻለ ግለሰብ ቢኖር፤ መቀጮ አይጣልበትም።
የአካል ጉዳተኛ መራጮች እገዛ ካሹ፤ ሊረዳቸው ከሚችል ጓደኛቸው ወይም ዘመዳቸው ጋር ሆነው ወይም የምርጫ ኮሚሽን ሠራተኛን እርዳታ በመጠየቅ ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ።
በአካል ተገኝተው ለመምረጥ የሚያውካቸው ከሆነም፤ በቅድመ ምርጫ ቀን፣ በፖስታ፣ እንደ አረጋውያን መጦሪያ፣ ሆስፒታሎች ባሉ መራጮች ባሉበት ድምፃቸውን እንዲሰጡ በሚፈቅዱ ተቋማት ወይም በስልክ መምረጥ ይችላሉ።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ነዋሪ ሆነው ለሽርሽር ወይም ለኑሮ ባሕር ማዶ ካሉ በምርጫ ወቅት በፖስታ ድምፃቸውን መስጠት ይችላሉ።
መረጃ በተለያዩ ቋንቋዎች
በምርጫ ሥፍራ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሠራተኞች ወይም በጎ ፈቃደኞች በቅድመ ምርጫ ዕለትና የምርጫ ዕለት በድምፅ መስጫ ሥፍራዎች የሚናገሯቸውን ቋንቋ ያሠፈረ ምልክት ልብሳቸው ላይ ተሰክቶ ወይም ተለጥፎ የሚታይ ሠራተኞች እገዛ ያደርጋሉ።
ኮሚሽኑ ዝርዝር ወረቀት ላይ ላልተካተቱ ቋንቋዎች ነፃ የስልክ አስተርጓሚ አገልግሎት ይሰጣል።
በምርጫ ሥፍራ ተጨማሪ የቋንቋ እገዛ ለሚሹ መራጮች የኮሚሽኑ ሠራተኛ ከብሔራዊ ወይም በጎ ፈቃደኞች ከብሔራዊ የትርጉምና አስተርጓሚ አገልግሎት ጋር ያገናኟቸዋል።
ምርጫዎችን አስመልክቶ በማኅበረሰባት ውስጥ የሚሰራጩ የሐሰተኛ መረጃዎችን ጎጂነት ለመቀነስ የኒው ሳውዝ ዌይልስ የምርጫ ኮሚሽን አሳስች ወይም ሐሰተኛ መረጃን ተከታትሎ የሚከላከልበት የሐሰት መረጃ ምዝገባ
ይጠቀማል።