በሕወሓት የተነሳ በአማራና አፋር ክልሎች ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውንና ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ የጉዳት ሰለባ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ገለፀ፣ በአጠቃላይ የደረሰው የጉዳት መጠን እየተጠና መሆኑንም ጠቅሷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ትናንት በሰጡት ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫ የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት የአዲስ አበባ ጉብኝት ወቅት ከጠሚር አብይ አህመድ ጋር በሁለቱ ሃገራትና ቀጠናዊ ጉዳዮች፣ በሕዳሴ ግድብና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ወቅታዊ ሁኔታም እንደመከሩ ገልፀዋል።
ቢልለኔ ሰፊ ትኩረት በሰጡት ወቅታዊው የኢትዮጵያ ሁኔታ በተለይ ሲገልፁ "አሸባሪው ሕወሓት አሁንም በአፋርና በአማራ ክልሎች ወረራውን በመቀጠል በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ነው " ብለዋል።
አክለውም፤ የደረሰው ጠቅላላ የጉዳት መጠን እየተጠና መሆኑን ገልጠው "የሰብዓዊ ድጋፉን ለማሳለጥ የሚያስችሉ ኮሚቴዎች በአፋርና በአማራ ክልሎች ተቋቁመው ከአጋር አካላት ጋር ሥራቸውን እየሰሩ ይገኛሉ" ሲሉም አስረድተዋል።
"ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ በአድልዖ ማውገዙን ማቆም አለበት፤ የሕወሓት ኃይሎች በሁለቱ ክልሎች ያደረሱትን ጥቃት ማውገዝ አለበት"ም ብለዋል።
ከአማራና አፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ሰዎች የሚደረገው ሰብአዊ ድጋፋ በቂ አለመሆኑንና አጋሮች የሚያደርጉትን ድጋፍ መጠን ከፍ እንዲያደርጉ የጠየቁት ቢልለኔ በሁለቱ ክልሎች የደረሰውን የጤና ተቋማት፣ ባንኮችና ሌሎች የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶች ውድመት በፎቶ አስደግፈው ለጋዜጠኞች አብራርተዋል፡፡
የብሔራዊ አደጋ ማስተባበሪያ፣ የአማራና አፋር ክልሎች የአደጋ እርዳታ ማስተባበሪያዎች ወደ ስራ መሰማራታቸውንና እርዳታ ለሚፈልጉ ሰዎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ቢልለኔ በትግራይ ክልልም የእርዳታ መኪኖች በህወኃት ዘረፋና መስተጓጎል ቢገጥማቸውም እርዳታው እየደረሰ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]