የገንዘብ ሚኒስቴር ለትግራይ ወረዳ ፣ ከተማና ቀበሌ የድጎማ በጀት የሚተላለፍበት አሠራር ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ አለ።
በሚኒስቴሩ የተዘጋጀው የበጀት ድጎማ አሠራር በሚቀጥለው ሣምንት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ ይደረጋል ብሏል።
በዚህም በጀቱ በወረዳ፣ ከተማና ቀበሌ አስተዳደር አካላት የባንክ ሂሳብ በኩል እንደሚተላለፍ ተገልጿል።
አስተዳደር አካላቱ የባንክ ሂሳብ ማስተላለፊያ ደብተር ካላቸው በዚያው በኩል ከሌላቸው ደግሞ አዲስ የባንክ ሂሳብ በመክፈት በጀቱ እንዲደርሳቸው ይደረጋል ነው የተባለው።
ሚኒስቴሩ የትግራይ ሕዝብ እንደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክልል ሕዝቦች የትምህርት ፣ የጤና ፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃ ፣ የምግብ ዋስትና እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ የሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ድጋፍ እንዲያገኙ ይደረጋል ብሏል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ እንዳሉት ከወረዳ ከተማና ቀበሌ የበጀት ድጋፍ አፈጻጸምን አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች የድጎማ በጀት የሚተላለፍበት አሠራር ዝርዝር በምክር ቤቱ ከጸደቀ በኋላ የሚገለጥ ይሆናል።
[ኢዜአ ]