የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በተሻሻለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከሰኞ ጀምሮ ይወያያሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ውይይቱ ከመጪው ሰኞ ነሐሴ 18 ቀን 2012 ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት በቢሾፍቱ ይካሔዳል።
በዚህ በዓመታዊው የአምባሳደሮች ሴሚናር ላይ ረቂቅ ፖሊሲው የበለጠ ትኩረት የሚያገኝ ይሁን እንጂ የኤምባሲዎችና ቆንስላዎች የሥራ አፈፃፀም ይገመገማል።
የወደፊት የስራ መመሪያዎችም እንደሚተላልፉ ተገልጧል።
አምባሳደር ዲና፤ በኮቪድ 19 የተነሳ አጠቃላይ የዲፕሎማሲ ሥራው ጫና ውስጥ መግባቱንና በዚህ የተነሳም እንደሚፈለገው እየተሠራ እንዳልሆነ አክለው ገልፀዋል።
በተለይ የቱሪዝም ሴክተሩ መዳከሙንና በዓረብ አገራት በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን ለመታደግ ወቅቱ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አብዛኞቹ ዜጎች በኢሚግሬሽን በኩል ያላለፉ፣ ህጋዊ ዶክመንት የሌላቸው በመሆናቸውና በውጭ አገራት ባሉን ኤምባሲዎችም ምዝገባ ስለማያደርጉ ለማገዝና ለመርዳት አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል ቃል አቀባዩ።
በዚህ አስቸጋሪ የኮቪድ 19 ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም በየአገራቱ ያሉ ኤምባሲዎችና ቆንስላዎች የዜጎችን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተሉ ጥብቅ መመሪያ በውጭ ጉዳይ በኩል ተሰጥቷል። እንደ አውሮፓ ህብረት ካሉ ተቋማት ጋርም እየሰራን ነው ሲሉ አክለዋል።
ቃል አቀባዩ ሌላው ያነሱት የህዳሴ ግድቡ ድርድር ጉዳይ ሲሆን አሁንም እንደቀጠለ ነው ብለዋል።
" በኢትዮጵያ በኩል በትጋት እየተደራደርን ነው። ድርድሩ ሂደት ላይ ነው አሁንም ፣ ውጤት ሲኖር በይፋ እናሳውቃለን" ብለዋል።