የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሬይኖርን በጽህፈት ቤታቸው ጠርተው ማብራሪያ ጠየቁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አምባሳደር ማይክ ሬይኖርን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው አስጠርተው ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ላይ በሰጡት አወዛጋቢ አስተያየት ዙሪያ ማብራሪያ ጠይቀዋል።
ትራምፕ አወዛጋቢውን አስተያየት የሰጡት ከሱዳን እና ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር የስልክ ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው፡፡
አቶ ገዱ በዚህ ወቅት የታላቁ ሕዳሴ ግድብን የዓባይን የውኃ ፍሰት እንደማይገታ ሁሉ ሕዳሴ ግድብንና የድርድሩን ሂደት አስመልክቶ የተሰጠው መግለጫ አሳሳችና ስሕተትንም የተላበሰ መሆኑን አበክረው አስታውቀዋል።
አክለውም፤ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል ጦርነት ቀስቃሽነት በስልጣን ላይ ካለ ፕሬዚደንት የማይጠበቅ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ አጋርነትና ስትራቴጂካዊ ግንኙነትን የማያንፀባርቅና ዓለም አቀፍ ሕግ በሚገዛቸው አገራት ግንኙነት ዘንድ ተቀባይነት ያለው አለመሆኑንም ገልጠዋል።
ሚኒስትሩ - ኢትዮጵያ ከቶውንም ባለፉትም ሆነ ለወደፊቱ በሉዓላዊነቷ ላይ በሚሰነዘሩ ማናቸውም ዛቻዎች የማትንበረከክና የሶስትዮሹንም ድርድር በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ ለመቀጠል የማታወላዳ መሆኑን ለአምባሳደሩ አስታውቀዋል።