የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ወ/ሪት ሶሊያና ሽመልስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በሐረሪ ክልል፣ በሶማሊ ክልል፣ በደቡብ ክልል ምዕራብ ኦሞ ዞን፣ በደቡብ ኦሞ ዞን፣ በቤንች ሸኮ ዞን፣ በሸካ ዞን፣ በጌዲዮ ዞን፣ በሃድያ ዞን፣ በጉራጌ ዞን ፣ በጋሞ ዞን፣ በካፋ ዞን፣ በወላይታ ዞን፣ በዳውሮ ዞን፣ በባስኬቶ ልዩ ወረዳ እና በኮንታ ልዩ ወረዳ ምርጫውን ዜጎች ማከናወን እንዲችሉ ሥራ ዝግ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
ምርጫው ከጠዋቱ 12:00 እስከ ምሽት 12:00 ይከናወናል ያሉት ሶልያና በ የምርጫ ክልሎች ቁሳቁሶች መድረሳቸውንና በቀሩ ጥቂት ጣቢያዎችም ከምርጫ ሰዓት በፊት ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል።
ለነገው ምርጫ መሰረታዊ የሆነ የፀጥታም ይሁን የቁሳቁስ ችግር እስካሁን አላጋጠምም ብለዋል ሶሊያና።
ምርጫውን 11 አገር በቀል ተቋማት 1690 ታዛቢዎቻቸውን የሚያሰማሩ ሲሆን ከእነዚህ አምስቱ በሁሉም አካባቢዎች የሚታዘቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በየሚሰሩባቸው አካባቢዎች ይታዘባሉ።
ሐሙስ ዕለት ምርጫ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች ውጪ ባሉት የአገሪቱ ክፍሎች ሰኔ 14/2013 ዓም አጠቃላይ ምርጫ መካሄዱና መንግስት መመስረት የሚያስችለውን አብዛኛውን ድምፅ ብልፅግና ፓርቲ ማሸነፉ ይታወሳል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]