ከትግራይ ክልል በስተቀር በመላው አገሪቱ የፊታችን ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም አጠቃላይ አገራዊ ምርጫ ሊካሄድ በተወሰነው መሰረት ብሔራዊ ምርጫ ቦርዱ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። የምርጫ ቁሳቁሶችም ምርጫ በሚደረግባቸው ጣቢያዎች ተሰራጭቷል ፣ ባልደረሰባቸው አካባቢዎችም በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኝ ቦርዱ አስታውቋል።
ዛሬ በስካይላይት ሆቴል ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ከድምፅ መስጫ አስቀድሞ ባሉት አራት የጥሞና ቀናትና በድምፅ መስጫው ቀን ሊደረጉ ስለማይገባቸው ተግባራት ምክክር አድርጓል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳስገነዘቡት " የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎችና ደጋፊዎቻቸው የጥሞና ቀን ትናንት ሰኔ 10 ቀን የጀመረ በመሆኑ ማንኛውም አይነት ቅስቀሳ ማድረግ አይፈቀድላቸውም። በየትኛውም የመገናኛ ዘዴ ስለፓርቲያቸው ፕሮግራም፣ ማኒፌስቶ፣ ዕቅድና ስኬቶቻቸው ዙሪያ ለህዝብ ማድረስም ሆነ ቃለ መጠይቆችን መስጠት ክልክል ነው" ብለዋል።
የመገናኛ ብዙሀን ተቋማትም ማንኛውንም ምርጫ ተኮር እንቅስቃሴዎችን ማሰራጨት ፣ በተጨማሪም የፓለቲካ ፓርቲ እጩዎችን አግኝተው ቃለ መጠይቆችን መስራት አይፈቀድላቸውም ሲሉ አክለዋል፡፡
ወይዘሪት ብርቱካን በተለይ በምርጫ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመቀነስ ሁሉም ፓርቲዎች " የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ፣ ምርጫና ስነ ምግባር ህግን " ተግባራዊ እንዲያደርጉ አፅንኦት ሰጥተዋል።
በስብሰባው የተሳተፉ የፓርቲ ተወካዮች በቅርቡ የጠቅላይ ሚኒስትሩና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝደንቱ ቃለ መጠይቅ በመንግስት ብዙኃን መገናኛ በተጀመረው የጥሞና ወቅት ሊተላለፍ ስለመሆኑ ማስታወቂያ ማስተላለፋቸው ተገቢ ባለመሆኑ ሊጠየቁ ይገባል ብለዋል። የኢዜማው ተወካይ አቶ አበበ አካሉ እንዳሉት ቃለ መጠይቁ ምንም እንኳን በብዙኃን መገናኛ ባለስልጣን እንዳይተላለፍ መታገዱ ተገቢ ቢሆንም ለገዥው ፓርቲ በወገኑ ሚዲያዎች የተደረገ በመሆኑ እንዲጠየቁ ቦርዱን አሳስበዋል።
በሌላ በኩል በአማራ ክልልና ደቡብ ክልል አንዳንድ የምርጫ ወረዳዎች ብልፅግና ፓርቲ ዛሬም ቅስቀሳ ሲያደርግ እንደነበር ኢዜማና የጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ወቅሰዋል።
የምርጫ ቦርዱ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ማንኛውም ፓርቲ ለጥሞና ጊዜ የተቀመጠውን ህግ ሊያከብር እንደሚገባ አሳስበው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ሆነ በጥሞና ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት በቦርዱ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
ምርጫው በተወዳዳሪዎችም ሆነ በመራጩ ህዝብ ዘንድ ምቹ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ትብብር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።
ሰኞ በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ 64 የፌደራል ምክር ቤቶች የምርጫ ክልሎች እንዲሁም 133 የክልል ምክር ቤቶች የምርጫ ክልሎች የማይሳተፉ ሲሆን በእነዚህ ምርጫ ክልሎች ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ምርጫው እንደሚከናወን ቦርዱ መግለፁ ይታወሳል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]