አብን የተወሰኑ የኦሮሚያ ብልፅግና አመራር አባላት ይቅርታ እንዲጠይቁት ለምርጫ ቦርድ አሳሰበ

*** የምርጫ ቦርድ የአብንን አቤቱታ አስመልክቶ "ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጽ 132 ንኡስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ህግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የስነምግባር ጥሰት ፈጽሞ አግኝቶታል" ሲል አስታወቀ።

NaMa

Belete Molla Getahun, Chairperson of National Movement of Amhara (NaMA). Source: BeleteMG

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በላከው የቅሬታ ደብዳቤ ቁጥር አብን198/01/13 በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ በተደረጉ ሰልፎች ላይ ስሜ ከዘር ፍጅት ወንጀል ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ተያይዞ በመቅረቡ የአካባቢው የብልፅግና ፓርቲ አመራር አባላት ይቅርታ እንዲጠይቁ ሲል ጠይቋል።

ንቅናቄው ጉዳዩን ሲዘረዝርም "የሰበታ ከተማ ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ እና የከተማዋ የብልፅግና ፓርቲ ሃላፊ አቶ ዋቀዮ አላኬ ድርጅታችንን በዘር ፍጅት ወንጀል ላይ በስፋት ከተሰማሩ ሽብርተኛ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ባወጣው በማጃመል፤ በክልሉ በሚኖረው ሰፊ አባላችንና ደጋፊአችን እንዲሁም አጠቃላይ ህዝባችን ላይ ሌላ ዙር ቀጣይ ጥፋትን ባረገዘ አኳኋን የፈረጀ ፍጹም አደገኛ ንግግር አድርገዋል" ብሏል።

ንግግሩንም በክልሉ ሚዲያ (OBN) እና በዋልታ ቲቪ መመልከቱን የገለጠው አብን "ይህንን ድርጊት በፈጸሙ የኦሮሚያ ብልፅኛ ፓርቲና አመራሮች ላይ ተገቢን የእርምት እርምጃ እንዲወሰድና እና በህዝባዊው ፓርቲያችን ላይ ለፈጸሙት አስነዋሪ ፍረጃ በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጥልን ስንል እንጠይቃለን" በማለት ምርጫ ቦርድን አሳስቧል።

 በተጨማሪም በዚሁ ዕለት ይህንኑ ሁነት አስመልክቶ ባለ ስድስት ነጥብ መግለጫ አውጥቷል።

1/ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ገደብ የለሽ የፖለቲካ ነውረኝነትና የዘረኝነት እንቅስቃሴ ለመቃወም በባልደራስ ፓርቲ ተጠርቶ የነበረውን ሕዝባዊ ሰልፍ በማንአለብኝነት የከለከለ መንግስት ለፖርቲ ፍጆታ ሲሆን ሰልፍ መጥራቱና መፍቀዱ፣

2/ በሰልፉ ላይ የጥላቻና የጥቃት ጥሪዎችን ሲመሩ የነበሩት በስምና በኋላፊነት የሚታወቁ የመንግስትና የብልፅግና ፖርቲ አመራሮች መሆናቸው፣

3/ በዛሬው ሰልፍ ላይ ጎልተው የተሰሙት ድምፆች የክልሉ አመራሮች በማኅበራዊ ድህረ-ገጽ ሲፅፏቸው የነበሩ ኃሳቦች ቀጥተኛ ግልባጭ መሆናቸው፣

4/ በዚህም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በአጠቃላይ ያለውን የፖለቲካ አፈና ወደተሟላ እርከን ለማሸጋገር በማሰብ አብን በክልሉ ውስጥ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታትና በክልሉ የሚኖረውን የአማራ ሕዝብና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በጭቆና ቀንበር ስር የማቆየት ዓላማ ያነገበ ተግባር መሆኑ፣

5/ በተለይም በዛሬው ሰልፍ ላይ በአማራ ሕዝብ ላይ በተደጋጋሚ የዘር ፍጅት ለመፈፀም ጽንፈኛ ኃይሎች መንደርደሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት «ነፍጠኛ» የሚለው ቃል በሰፊው ሲገለፅ የነበረና በግልፅም «ነፍጠኛ ይውጣ» የሚል ኃሳብ ሲሰማ የነበረ መሆኑ፣

6/ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃላፊነት የጎደላቸው ጽንፈኛ አመራሮች በአማራ ሕዝብ ላይ እየደረሰ ላለው ጥቃት ሽፋን በመስጠትና በቀጥታ በመሳተፍ እንደሚያስፈፅሙ የተረጋገጠ ጉዳይ ሆኖ እያለ በታየው ደረጃ የተላለፈውን የጥላቻና የጥቃት ጥሪ የመንግስት ሚዲያዎች መዘገባቸው እና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርም እርምት መስጠት እየተገባቸው ቡራኬ መስጠታቸው እጅግ አሳዛኝ የሆነና በቀጣዩ የአገራችን የፖለቲካ ኺደት ላይም ከፍተኛ ስጋትን እንደሚፈጥር መረዳት ይቻላል።

 ይህንኑ የአብንን አቤቱታ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በማግሥቱ ጥር 26 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጠው ምላሽ፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) “ፓርቲያችን ያለአግባብ ተወንጅሏል፣ ይህም ፓርቲዎች የፈረሙትን የጋራ የስነምግባር ደንብ የጣሰ ነው” ሲል አቤቱታውን ለቦርዱ ማቅረቡን ገልጦ በአሜሪካ ድምጽ፣ በዋልታ፣ በፋና፣ በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ እንዲሁም በነዚሁ ሚዲያዎች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በቀጥታ የተላለፉ መልእክቶችን መመልከቱን ጠቁሟል።

የምልከታ ግንዛቤውንም ሲያስረዳ፤

- ሠልፎቹ በዋልታ ቴሌቪዥን እና በኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በቀጥታ መተላለፋቸውን እንዲሁም የመንግስት አመራር አካላት፣ የብልፅግና ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎች መሳተፋቸውን ተረድቷል።

- ከሚዲያዎቹ በቀጥታ ከመተላለፉም በተጨማሪ የተለያዩ የመንግስት አመራር አባላት በሰልፎቹ ላይ ያደረጓቸውን ንግግሮች ተመልክቷል።

- በሰልፎቹ የተለያዩ መፈክሮች፣ በተወሰኑ የመንግስት የዞን፣ የከተማ አስተዳድር አመራር አካላት  እና ብልጽግና ፓርቲ ሃላፊዎች ንግግሮች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተመዘገቡ እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን የመረጡ ፓርቲዎች በአሉታዊ መልኩ መነሳታቸውን ተገንዝቧል

ያለ ሲሆን፤ አያይዞም "እነዚህ ሰልፎቹ ላይ የተነሱ ንግግሮች እና መፈክሮች በህጋዊነት ተመዝግበው፣ በፖለቲካ ፓርቲነት የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችን ማለትም አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በአመፃ ተግባር በመሳተፍ ከምርጫ ቦርድ ከተሰረዘው ጁንታ በማለት ከሚጠሩ ህወሃት ፓርቲ ጋር አንድ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ጠላት ናቸው ብሎ በመፈረጅ እና ህገወጥ ናቸው በማለት የምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር ህግ 1162/2011 ላይ ያሉ ድንጋጌዎችን ጥሰዋል" ሲል ገልጧል።

ይህ በመሆኑም "ቦርዱ ሰልፎቹ ላይ የተንጸባረቁት ንግግሮች እና መፈክሮች በአዋጁ አንቀጽ 132 ንኡስ 2(ሀ) ላይ የተጠቀሰውን ስም የሚያጠፋ ንግግርን ክልከላ ድንጋጌ አንዲሁም በዚሁ ህግ አንቀጽ 143 (2) ላይ የተጠቀሰውን ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት እንዳያሰራጩ ስጋት እና ፍርሀት የመፍጠር የስነምግባር ጥሰት ፈጽሞ አግኝቶታል። 

"ከዚህም በተጨማሪ  ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ገዥው ፓርቲ በጋራ ተስማምተው በፈረሙት የቃልኪዳን ሰነድ አንቀጽ 8 ንኡስ አንቀጽ 1 ላይ የተጠቀሰውን “የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በየትኛውም ጉዳይ ላይ ሊኖር የሚችል የዓላማ፣ የሃሳብ ወይም የዘር ልዩነትን፣ ወይም ሌላ ምክንያት መሰረት በማድረግ የሌሎች ፓርቲዎችን መብቶች የሚፃረሩ ወይም የሚያጣብቡ ድርጊቶችን ከመፈፀም የመቆጠብ ግዴታ አለባቸው” ሲል አሳስቧል። 

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ለወደፊቱ ቢከሰቱ ቦርዱ "በምርጫ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ስነምግባር ህግ 1162/2011 እና ተያያዥ መመሪያዎች መሰረት የፓርቲዎች የቅስቀሳ የንግግር እና ሌሎች ለህዝብ የሚያሰራጯቸውን መልእክቶች ላይ ክትትል በማድረግ አስፈላጊውን እስከእጩ መሰረዝ የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያሳውቃል" ሲል አጽንዖት ሰጥቶ አስጠንቅቋል።

 

 

 

 

 


Share

Published

Updated

By Stringer Report

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service
አብን የተወሰኑ የኦሮሚያ ብልፅግና አመራር አባላት ይቅርታ እንዲጠይቁት ለምርጫ ቦርድ አሳሰበ | SBS Amharic