የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ ለዘመናት አብረው የኖሩ ፣ ክፉና ደጉን በጋራ ያሳለፉ፣ የተዋለዱና የተዋሃዱ ሕዝቦች ናቸው። ኃቁ ይህ ሆኖ እያለ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ በተፈጠሩ ጥራዝ ነጠቅና በአማራ ጥላቻ በሰከሩ ብሔርተኞች የሁለቱን ሕዝቦች ግንኙነት የጨቋኝና የተጨቋኝ አለፍ ሲልም የቅኝ ገዢና ተገዢ አድርገው በማቅረብ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የዘለቀውን ጠንካራ ትስስር ለማላላት በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
የተሰራው ሥራ ያክል የሁለቱን ሕዝቦች ትስስር በዘላቂነት ማላላት ባይቻለም በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ በተደበቁ የዚህ የጥላቻ ትርክት የሰከሩ ቡድኖች አማካኝነት ባለፉት 30 ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ በርካታ የዘር ፍጅቶች ተፈፅመዋል፤ እየተፈፀሙም ይገኛል፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬም እንደትላንቱ የአማራ ሕዝብ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር በጋራ አብሮ እየኖረ ነው::
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ይህ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ስህተት እንደነበር፣ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚፈፀመውም ፍጅትም ተገቢ አለመሆኑን የሚገልፁ አንዳንድ የኦሮሞ ፓለቲከኞች ቢኖሩም አሁንም በአማራ ሕዝብ ላይ ለሌላ ዙር እልቂት የሚጋብዝ፣ ሁለቱን ሕዝቦች የሚያራርቅ፣ የሐሰት ትርክት የሚያራምዱና በአደባባይ ሕዝብን የሚያነሳሱ በመኖራቸው የኦሮሞ ሕዝብ መሰል አካላትን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ሊገስፃቸውና ሊያርማቸው ይገባል፡፡ መንግስትም መሰል የጥላቻ ንግግሮችን በሚያደርጉና ሕዝብን በሕዝብ ላይ በሚያነሳሱ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ ማስገንዘብ እንፈልጋለን፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የአማራና የኦሮሞ ሕዝቦች ካላቸው የዘመናት ትስስርና መዋሃድ የተነሳ የወደፊት እጣ ፈንታቸው በእጅጉ የተሳሰረ ነው ብሎ ያምናል። የሁለቱ ሕዝቦች ጥቅሞችና ህልሞችም የግድ የሚጋጩ ሳይሆኑ በሰለጠነ፣ በሰከነና ስርዓት ባለው ውይይትና በሰጥቶ መቀበል መርኅ በተቃኘ ድርድር ሁለቱም ሕዝቦች አሸናፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል እንዳለ ይገነዘባል። ከዚህ በተቃራኒ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል በልሂቃን ቆስቋሽነት ሊፈጠር የሚችል ግጭትና አለመግባባት ለአገራችንም ሆነ ለቀጣናው አለመረጋጋት በመፍጠር ከፍተኛ ጥፋት ሊያደርስ የሚችል እንደሆነም አብን ያምናል፡፡
በዚህ አጋጣሚ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ከተራማጅ የኦሮሞ የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ጥላቻንና ጥርጣሬን ከሚዘሩ አማራ ጠል ኃይሎች እጅ ወጥቶ ወደ ሰለጠነና የሁለቱንም ሕዝቦች ተጠቃሚነት ወደሚያረጋግጥ ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ለማሳደግ እየሰራ ሲሆን በቅርቡ በሁለቱ ሕዝቦች የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የተፈረመው ስምምነት ወደ ተግባር እንዲለወጥ ብሎም የሁለቱ ሕዝቦች ልሂቃንና ፖለቲከኞችም የሕዝቦቻችንን ታላቅነት ለሚመጥን ግንኙነትና ድርድር ዝግጁነታችሁን በተግባር እንድታሳዬ አብን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ምንም እንኳ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል እንደ ከአሁን ቀደሙ በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ባይቻልም በዓሉ ሲከበር የከኮሮና ወረርሽኝን በማያባብስና በሕዝቦች መካከል ልዩነትን በማይፈጥር መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አብን ማሳሰብ ይወዳል!
በድጋሚ መልካም በዓል!
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)