የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ስድስተኛ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ የተለያዩ መመሪያዎችን እያፀደቀ ነው፡፡ ከእነዚህ የምርጫ መመሪያዎች አንዱ የሆነውን በምርጫ ሂደት ወቅት የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ አውጥቶ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የሕዝብ አስተያየት ክፍት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የረቂቅ መመሪያው ዋና ዓላማ በቅድመ ምርጫ፣ በድምፅ መስጫ ቀን እና በድህረ ምርጫ ወቅት ከምርጫ ጋር ተያያዥ ተግባራት ሁሉ የቫይረሱን ስርጭት እንዳይጨምር ማድረግ ነው ተብሏል፡፡
ረቂቅ መመሪያው ለቦርዱ፣ ለምርጫ ባለድርሻ አካላት እና አስፈፃሚዎች ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ያስፈልጋሉ በሚባሉ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ረቂቅ መመሪያውን ከሕዝብ በሚሰበሰብ ገንቢ አስተያየት ለማዳበር ይረዳ ዘንድ ለአንድ ሳምንት ለሚቆይ ጊዜ ክፍት ተደርጓል፡፡ ረቂቅ መመሪያው ከዛሬ ጀምሮ ለሕዝብ አስተያየት ክፍት መሆኑን የገለፀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በረቂቁ ዙሪያ ለሚኖር ሀሳብና አስተያየት በኢሜል አድራሻ legal@nebe.org እንዲሁም በቦርዱ ገጽ መልዕክት ማስቀመጫ አማካኝነት መላክ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
ለተጨማሪ መረጃ:- ረቂቅ መመሪያውን ለማግኘት ተከታዩን ማስፈንጠሪያ በመጠቀም መጫን ይቻላል፡፡ https://urldefense.com/v3/__https://bit.ly/3ofdkAn__;!!MiK4Rck!B0A1vsGswyI26UFseFez3HrowKqD5CAFzUp9uROxExjWHX6_BSoMyFd6QycbgzwVZhPA$
[ምርጫ ቦርድ]