የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዳስታወቀው "በህጋዊነት የተመዘገቡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን ወስደዋል" ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 6ተኛው አገር አቀፍ ምርጫን ለማከናወን በጊዜ ሰሌዳው ላይ ካስቀመጣቸው ተግባራት መካከል አንደኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ምልክቶቻቸውን የሚመርጡበት/ የሚያስገቡበት መርሃ ግብር ነው።
በዚሁ የጊዜ ሰሌዳ መሰረትም ከጥር 13 ቀን እስከ ጥር 24 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ፓርቲዎች ምልክት የሚያስገቡበት እና ቦርዱ አጣርቶ እንደሚያፀድቅ ተገልጿል።
ቦርዱ ይፋ እንዳደረገው በህጋዊነት የተመዘገቡ ሲል የገለፃቸው ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ መወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን መርጠው ያስገቡ ሲሆን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ዛሬ ማፅደቁን ገልጿል።
በዚህም መሰረት ምልክቶቻቸው በቦርዱ የፀደቀላቸው 49 የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ይፋ ሆነዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ ]